በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከ40 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ 46 ሚሊዮን 620 ሺህ ብር በላይ ከመንግሥት ሊወጣ የሚችለውን ለማዳን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት አስታወቀ

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከ40 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ 46 ሚሊዮን 620 ሺህ ብር በላይ ከመንግሥት ሊወጣ የሚችለውን ለማዳን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት አስታወቀ

”የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የአቅመ ደካማ አረጋውያንን ቤት በመስራት ደም በመለገስና በተለያዩ ስራዎች የዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያው የተገኙት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኪበሞ ሰለሞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከጥንት ጀምሮ የኖረ ዕሴት መሆኑን ጠቅሰው ይህም ዕሴት እያዳበረ መጥቶ ከባለፉት ዓመታት ጀምሮ የበርካቶችን ህይወት መቀየር ተችሏል ብለዋል።

በዘንድሮ የ2018 ዓ.ም በክረምት በጎ ፈቃድ ስራ በከተማ አስተዳደር ባሉ ሁሉም ቀበሌያት በ15 የስራ ዘርፎች ከ40 ሺህ 250 በላይ ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ ከ86 ሺህ 600 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

በበጎ ፈቃድ ወጣቶች አማካኝነት የአቅመ-ደካሞችንና የአረጋውያንን ቤት ማደስና መገንባት፣ አረንጓዴ አሻራ የማኖር፣ ደም ልገሳ፣ በከተማ ጽዳትና ውበት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠትና በመሳሳሉት ከፍተኛ ጠቀሜታ ባላቸው ዘርፎች እንደሚሳተፉ አስረድተዋል።

በተለይም የመንግሥት ትኩረት አቅጣጫ በሆኑ በዲጂታል መታወቂያ እና ኢትዮ ኮደርስ ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠርና ተጠቃሚ እንዲሆን በማስቻል በትኩረት እንደሚሰራ የገለፁት አቶ ኪበሞ፤ በከተማው ባሉ ቀበሌያት 7 አዳዲስ የብሎኬት ቤት ለመገንባትና 7 ቤቶችን ለማደስ ስራው መጀመሩን ጠቁመዋል።

ለቀጣይ ወራት በሚካሄዳው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመንግሥት ይወጣ የነበረውን ከ46 ሚሊዮን 620 ሺህ ብር በላይ ወጪ ለማዳን መታቀዱን የጽ/ቤት ኃላፊው አስገንዝበዋል።

በመላው ሀገሪቱ ”የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ በማንገብ የተጀመረው ተግባር ሁላችንም ብንረዳዳና የአቅማችንን ብናደርግ ለበርካቶች መድረስ እንደሚቻል ውጤት የታየበት በመሆኑ ይህንንም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ያሉት ደግሞ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊና በፕሮግራሙ የቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ በረከት ታደሰ ናቸው።

በፕሮግራሙ የተገኙት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የአብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፋንታሁን ሊረንሶ፤ ኢንሼቲቭ መልክ ላለፉት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማህበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ በርካቶችን ያገዘ ተግባር መሆኑን አንስተው በክረምቱ ወቅት የተጀመረው የወጣቶች በጎ ፈቃድ ስራ ከግብ እንዲደርስና የታሰበውን ለውጥ እንዲያመጣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በዕለቱም በሴች ዱና ቀበሌ የአንድ አረጋዊ ቤት ግንባታ የተጀመረ ሲሆን የከተማ ጽዳት የደም ልገሳና ሌሎች የበጎ ፈቃድ ስራዎች ተካሂዷል።

ያነጋገርናቸው ወጣቶች በበኩላቸው በእንደዚህ ዓይነት መሰል በጎ ፈቃድ ስራዎች መሳተፍ በራስ ተነሳሽነት የሚፈጸም በመሆኑ ልዩ ደስታ እንደሚፈጥር ገልፀው ወጣቶች ጊዜያቸውን ለማህበረሰባቸው በሚጠቅሙ በመሰል አገልግሎቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን