የቀቤና ልዩ ወረዳ ማህበረሰብ የልማት ፍላጎት ማሟላት የሚቻለው ግብርና ታክስ በታማኝነትና በወቅቱ መክፈል ሲቻል መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 02/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የልዩ ወረዳው ማህበረሰብ የልማት ፍላጎት ማሟላት የሚቻለው ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብርና ታክስ በታማኝነትና በወቅቱ መክፈል ሲችሉ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በሀሩ ዲጋ ገለጹ።
በልዩ ወረዳው በ2018 በጀት አመት ለመሰብሰብ ከታቀደው ገቢ አስካሁን 255 ሚሊየን 778 ሺህ ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 125 በመቶ ማሳካት መቻሉም ተጠቁሟል።
የሀገር እድገትና ልማት ያለ ግብርና ታክስ አይታሰብም ያሉት ሃላፊው በልዩ ወረዳው በ2018 በጀት አመት በመደበኛና በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዘርፍ 204 ሚሊየን 632 ሺህ ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ አስካሁን 255 ሚሊየን 778 ሺህ ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።
በዚህም የዕቅዱን 125 በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን፤ የተሰበሰበው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ95 ሚሊየን 408 ሺህ ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አቶ በሀሩ ተናግረዋል።
ለገቢ አሰባሰቡ ስኬታማነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀትና የጋራ ተግባቦት በመፍጠር በልዩ ወረዳው የሚመረቱ የጫትና የአጠና ምርት እንዲሁም የገጠር መሬት እና ሌሎችም የገቢ አማራጮችን በአግባቡ አሟጦ መሰብሰብ በመቻሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለግብር ከፋዮችና ለባለድርሻ አካላት በየወቅቱ የግንዛቤ ማስጨበጫና የንቅናቄ መድረኮች ከመፍጠር ባሻገር በየጊዜው ተሻሽለው የሚመጡ የግብርና ታክስ አዋጆችንና ደንቦችን በአግባቡ በመተግበር ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
ለውጤታማነቱ የተቋሙ ባለሙያዎችና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ሃላፊው፥ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የቫት ግብር ከፋዮች በታማኝነት ደረሰኝ ከመሰጠት ጋር በተያያዘ ውስንነት በመኖሩ በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የልዩ ወረዳው የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የሥራ ግብር አሰባሰብና የ2019 በጀት አመት የንግድ ፍቃድ እድሳት በይፋ መጀመሩን የገለፁት አቶ በሀሩ፥ የደረጃ “ሀ” የገቢ አሰባሰብ ሂደት ከሳምንት በኃላ እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ በሚቀጥሉት 5 ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እንዲቻል አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር መገባቱንም ተናግረዋል።
የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብርና ታክስ የመክፈያ ወቅቱ ሳይጠናቀቅ በመክፈል ካላስፈላጊ ቅጣትና እንግልት ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው በማሳሰብ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለግብር አሰባሰቡ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በ2018 ከደረጃ “ለ” ከ13 ሺህ 300 ግብር ከፋዮች ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል – በሀላባ ዞን የቁሊቶ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የመንግሥትን ወጪና የልማት ፍላጎት ለመሸፈን በ2019 በጀት ዓመት 14 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ገለጸ
በዞኑ ከ11ሺ 268 የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከ56.8 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለፀ