በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ የተመራ ልዑክ በጂንካ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን መረቁ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ ዋና አፈ ጉባኤ የተመራው የአመራሮች ቡድን በጂንካ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ በሚገኙ ቀበሌያት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ጉብኝትና የምረቃ መርሃ ግብር አካሂደዋል።
ቡድኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማስፋፊያ የመብራት ተጠቃሚ ባደረጋት የባዘት ቀበሌ በመገኘት አገልግሎቱን በይፋ መርቋል።
በተመሳሳይም ኩሬ ቀበሌ በማቅናት በቀበሌው እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ተግባራት ያሉበትን ሁኔታ ተመልክቷል።
የቀበሌውን የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብርም ተከናውኗል።
በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ደግፌ ጌታቸው የኩሬ ነዋሪዎች የመብራት ጥያቄ ከደርግ ዘመን የጀመረ መሆኑን አስታውሰዋል።
ረጅም ጊዜ ያስቆጠረው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ስራ መጀመሩን ጠቅሰው ለዚህም ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የመስመር ዝርጋታ ስራ እንዲጀመር ከስምምነት መደረሱን ተከትሎ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል።
ስራው በጅምር ላይ ይገኛል ያሉት ከንቲባው በአካባቢው የሚነሱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥያቄን ጨምሮ የመንገድ ጉዳይ በሂደት ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል።
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው በዞኑ የሚነሱ በርካታ የመልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን ጠቁመው፥ መንግስት እንደ አንገብጋቢነታቸውና ደረጃ በደረጃ መልስ ለመስጠት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የረዥም ጊዜ ጥያቄ የሆነው የኩሬ ቀበሌም ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተራው ደርሶ ምላሽ የሚሰጥበት ፕሮጀክት በመጀመሩ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
የመብራት ችግር ከፍተኛ ምሬት ሲፈጥር የቆዬ በመሆኑ የዞኑና ከተማ አስተዳደሩ ከፌደራል መንግስት ከመጠበቅ የዞኑና ከተማ አስተዳደሩ በመነጋገር ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ ስራው እንዲጀመር መደረጉን አብራርተዋል።
አስፈላጊ ክፍያዎች በመጠናቀቃቸው በቅርብ ወራት የመብራት አገልግሎት በአካባቢው ተደራሽ እንደሚሆን አትጠራጠሩ ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
አምራቹ የኩሬ አካባቢ የዞኑ ኢኮኖሚ መሰረት በመሆኑ የመብራት ጥያቄው መዘግየት ቁጭት የሚፈጥር በመሆኑ መንግስ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት የመስመር ዝርጋታ ስራ ማስጀመሩን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ም/ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ናቸው።
ሰው ተኮር የሆነው መንግስታችን ቃልን በተግባር የመቀየር መርሁ ከንግግር ለተሻገረ ተጨባጭ ተግባሩ ይህ የኩሬ ቀበሌው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ምዕራፍ ጅማሬ ማሳያ ይሆናል ብለዋል።
በዞኑና ከተማ አስተዳደሩ ቅንጅታዊ ውሳኔ የተጀመረው ስራ በሁለትና ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ የአካባቢውን የጨለማ ዘመን እንደሚታደግም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ለዚህም በአንድነት መስራት ወሳኝነት አለው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤው በመነቃቀፍና መረጋገም የሚባክን ጊዜ ሳይኖር ለለውጥ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የአረንጓዴ አሻራ ስራ በአካባቢው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን በሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ ደን ልማትና አከባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ገለፀ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተመራ የኣሪ ዞን ብልጽግና ፓርቲና የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በሰሜን ኣሪ ወረዳ በመገኘት የተለያዩ የመሰረተ ልማት ተግባራትን መረቀ
ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባው የጂንካ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት የተጠርጣሪ ማቆያና የቢሮ ህንጻ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው በተገኙበት በደማቅ ሥነ ስርዓት በይፋ ተመረቀ