ከ5ሺህ 500 ባላይ ወጣቶችን በመደራጀት የስራ ዕድል መፍጠሩን የሌሞ ወረዳ ስራ ዕድል ፈጠረ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ገለፀ

ከ5ሺህ 500 ባላይ ወጣቶችን በመደራጀት የስራ ዕድል መፍጠሩን የሌሞ ወረዳ ስራ ዕድል ፈጠረ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ገለፀ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ5ሺህ 500 ባላይ ወጣቶችን በ111ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት የስራ ዕድል መፍጠሩን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ ስራ ዕድል ፈጠረ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት አስታወቀ።

በወረዳው በተለያዩ የስራ መስኮች የተሠማሩ ወጣቶች በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን ተግተው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በሌሞ ወረዳ ከሚገኙ ቀበሌዎች ከ6ሺህ 400 ባላይ ስራ አጥ ወጣቶችን በመለየት 5ሺህ 552 ወጣቶችን በከተማና በገጠር ግብርና እንዲሁም በማንፋክቸርንግ የስራ ዘርፎች መሰማራት መቻሉን የሌሞ ወረዳ ስራ ዕድል ፈጠረና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብነት አበራ ገልጸዋል።

እነዚህ ወጣቶች በ111 ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ መሆናቸውን ጠቁመው፥ 4 ሺህ 252 ወጣቶች በቋሚነት 1ሺህ 300 ወጣቶች ደግሞ በጊዜያዊነት የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።

ወጣቶቹም በስፋት የተሠማሩት በግብርናው ዘርፍ ሲሆን የዶሮ እርባታ፣ ንብ ማነብ፣ ችግኝ ማፍላት፣ የጓሮ አትክልት ማምረትና ሌሎችም የእርሻ ሰብል ተግባራት ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸውም ብለዋል።

25 ሄክታር የወል እና 11 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ደግሞ በኪራይ ወጣቶቹ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ

እንደተዘጋጀላቸው አቶ አብነት ገልጸዋል።

የስራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ወጣቶች 1ሚሊየን 1መቶ ሺህ ብር በመንግሥት በኩል የተመቻቸ ሲሆን ከ 37 ሚሊየን 500 ሺህ ብር በላይ በጀት በፕሮጀክቶች በኩል ድጋፍ መደረጉን ኃላፊው አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፕሮጀክቶቹ በግብርና ለተሠማሩ ወጣቶች 50 ኩንታል የድንች ዘርና በዶሮ እርባታ ለተሠማሩ ወጣቶች ጫጩቶችን እየቀረበ መሆኑንም አክለዋል።

ለኢንተርፕራይዞች ስራ ማነቆ የሆነውን የገበያ ችግር ለመፍታት ከተለያዩ አካላት ጋር በመነጋገር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

ወጣቶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ ጽ/ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብነት፥ ወጣቱ ትውልድ በስደት ጉዞ የበረሃ ሲሳይ መሆኑን ትቶ ለመለወጥ በሀገር ጠንክሮ እንዲሠራ መክረዋል።

በወረዳው ቡቁና ቸቻዬንቾ ቀበሌ “ምሻሜ” በሚል ስያሜ ለ10 በማህበር ተደራጅተው በጓሮ አትክልት ስራ የተሠማሩ ወጣቶች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ዘጸአት ክባሞ ገልጿል።

በዚሁ ቀበሌ “ማሶ ስንዳ” በሚል ማህበር ለአስር ተደራጅተው ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ ያለቸውን የዛፍ ችግኞችን እያዘጋጁ መሆናቸውን የማህበሩ አስተባባሪ ወጣት ፍጹም ፍሬ ህይወት ተናግረዋል።

የባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ እንዳልተለያቸው የጠቆሙት ወጣቶቹ በአሁኑ ጊዜ የውሃና ሌሎችም አማራጮችን ለመጠቀም ወደ ሆሳዕና ከተማ አከባቢ መጥተው እያመረቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ በአሁኑ ወቅት ራሳቸውን ከመደጎም ጎን ለጎን ለሌሎች ወጣቶችም የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረው፥ ወጣቶች ስደትን ከመሻት ይልቅ በሀገር ሰርቶ ለመለወጥ መዘጋጀት አለባቸውም ብለዋል።

ዘጋቢ፡ መንግሥቱ ፊጣሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን