በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተመራ የኣሪ ዞን ብልጽግና ፓርቲና የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በሰሜን ኣሪ ወረዳ በመገኘት የተለያዩ የመሰረተ ልማት ተግባራትን መረቀ
ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል የገሊላ ከተማን ከጎዛ ከተማ የሚያገናኘው የሳላ ወንዝ ድልድይን ጨምሮ አላጊቻ ጎዛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።
ልዑካን ቡድኑ ከጉብኚቱ ባሻገርም የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በይፋ ተመርቀው አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል።
ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከልም ከ47 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የሰሜን ኣሪ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው የገሊላ ከተማን ከጎዛ ታዳጊ ማዘጋጃ ቤት ጋር የሚያገናኘው የሳላ ወንዝ ድልድይ ይገኝበታል።
ሌላኛው የጎዛ አላጊቻ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕጀክት ሲሆን ለግንባታው 9.5 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎጎበታል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ በወረዳው፣ በዞኑና በክልሉ ውኃና ኢነርጅ ቢሮ እንዲሁም በዋን ዋሽ ናሽናል ፕሮግራም 2 አማካይነት የተከናወነ መሆኑ ታውቋል።
በዚሁ ምረቃ ወቅት ንግግር ያደረጉት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጎሳዬ ጉሳር፤ ህዝቡ በትዕግስት ከሚጠባበቃቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ዛሬ የተመረቁት የረጅም ጌዜ ጥያቄውን የመለሱ ናቸው ብለዋል።
የጎዛ ገሊላ መንገድ ግንባታን ጨምሮ በቀጣይ ሌሎች የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙ ዘንድ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
ታታሪው የጎዛ ህዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ባገኙበት መድረክ ንግግር በማድረጌ ኩራት ተሰምቶኛል ያሉት ደግሞ የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ ናቸው።
መንግስት ለበርካታ ህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው በሂደትም በአጭር ጊዜ ከተማው የኤሌክትሪክ አገልግሎል እንዲያገኝ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የመድረኩ የክብር እንግዳ የሆኑት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው፤ መንግስት ቀድሞ የነበሩ ስብራቶችን ለመጠገን አኩሪ ተግባራትን እየፈጸመ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ለአመታት የዘለቁ የህዝብ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገር ያላትን የኢኮኖሚያዊ አቅም በፍትሀዊነት ለማዳረስ በሚያደርገው ጥረት የሰሜን ኣሪ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት አጋጣሚ ታሪካዊና ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
ቃልን በተግባር የሚል መርህ ያለው መንግስታችን ቃሉን በተግባር በማሳየት ለምረቃ እንዳበቃቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች ሁሉ በቀጣይም ሌሎች የህዝብ ጥያቄዎች መልስ ያገኙ ዘንድ ቃሉን በተግባሩ ለማረጋገጥ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባው የጂንካ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት የተጠርጣሪ ማቆያና የቢሮ ህንጻ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው በተገኙበት በደማቅ ሥነ ስርዓት በይፋ ተመረቀ
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ቢሊዮን 4 መቶ 21 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ
በትራንስፕርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየተደረገ ባለው ከታሪፍ በላይ ጭማሪ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች እየተጋለጥን ነው ሲሉ በወልቂጤ ከተማ መናኽሪያ አግኝተን ያነጋገርናቸው ተሳፋሪዎች ተናገሩ