ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ቢሊዮን 4 መቶ 21 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ቢሊዮን 4 መቶ 21 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ

መምሪያው የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ገምግሟል።

የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ጉጃ፤ መንግስት የገቢ አሰባሰብ ሂደትን ዘመናዊ፣ ፍትሐዊና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ የሪፎርም ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት የግብር አሰባሰብ ሂደትን ከወረቀት ነጻ የዲጂታል አሰራርን ለማሥፈን ያደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለመሠብሰብ ከታቀደው ጠቅላላ ገቢ 1 ቢሊዮን 5 መቶ 68 ሚሊዮን 897 ሺህ ብር ገቢ ከ1 ቢሊዮን 4 መቶ 21 ሚሊዮን ብር በላይ የተሠበሠበ ሲሆን በዚህም የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

ይህ አፈፃፀም ካለፈዉ ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በገንዘብ 4 መቶ 92 ሚሊዮን 205 ሺህ ብር እንዲሁም 52.93 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አብራርተዋል።

የታክስ ማጭበርበር እና ሥወራን ለመክላከል በተዘረጋዉ አሰራር መሠረት በዞኑ የሚገኙ 3 መቶ 56 የደረጃ “ሀ” ግብር ክፋዮች በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት 3 ሺህ 267 መለያ ኮድ ያለው ደረሰኝ አሳትመዉ እንዲጠቀሙ ተደርጓል ብለዋል።

ከገቢ ስወራ ጋር ተያይዞ በቁጥር 10 ግብር ክፋዮች ላይ መረጃዎችን በማደራጀት የድንገተኛ ክትትል ሥራ ለመስራት ታቅዶ 5 ግብር ከፋዮች ላይ ድንገተኛ ክትትል በመስራት በህግ እንዲጠየቁ መደረጉን ጠቁመዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው፤ መንግስት የህብረተሠቡን የልማት ጥያቄ በተገቢው መንገድ መመለስ የሚያስችለው ግብር በአግባቡና በወቅቱ ሲሰበሰብ በመሆኑ በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በአንዳንድ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተስተዋለ ያለው የገቢ አሰባሰብ ዝቅተኛ መሆን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው ችግሩን ከሥሩ ለይቶ በተቀሩት ጥቂት ወራት ተገቢው ግብር መሠብሠብ እንደሚገባው ገልጸዋል።

ተሳታፊ የገቢ ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት በተለይ በከተሞች የመደበኛውን ገቢ አሰባሰብ ዝቅተኛ እንዲሆን ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶች አሰባሰብ ከፍተኛ ውስንነት የታየበት መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉ በቀጣይም ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ገልጸዋል።

ወቅቱን የጠበቀ የኦዲት ተግባርና ግኝቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ረገድም ሠፊ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው፤ የተበተነ የፍቃድ አሠጣጥ ሂደት ለመንግስት የሚገባውን ግብር የሚቀንስ ነው ብለዋል።

በሳውላ ከተማ አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግዶችን ለመቆጣጠር የሠላምና የመልካም አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ላለፉት ጊዜያት የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች ገቢ መሬትና መሬት ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ መመሥረቱ ዛሬ የመሬት አስተዳደር ተቋም በአዲስ ተደራጅቶ ለብቻው መውጣቱ ፈተና ውስጥ እንዳስገባው ጠቁመዋል።

ወቅታዊ የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብን ተከትሎ ህገ ወጥ የንግድ አዝማሚያዎችና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ የንግዱ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

በገቢ ዙሪያ የህግ የበላይነትን ተግባራዊ በማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ጉጃና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ማብራሪያና የሥራ መመሪያዎችን ሰጥተዋል።

የገቢ አማራጮች ላይ ልዩ ትኩረት መሥጠት እንደሚገባም ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን