በትራንስፕርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየተደረገ ባለው ከታሪፍ በላይ ጭማሪ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች እየተጋለጥን ነው ሲሉ በወልቂጤ ከተማ መናኽሪያ አግኝተን ያነጋገርናቸው ተሳፋሪዎች ተናገሩ

በትራንስፕርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየተደረገ ባለው ከታሪፍ በላይ ጭማሪ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች እየተጋለጥን ነው ሲሉ በወልቂጤ ከተማ መናኽሪያ አግኝተን ያነጋገርናቸው ተሳፋሪዎች ተናገሩ

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት በበኩሉ የነዳጅ እጥረት ምክንያት በማድረግ ከታሪፍ እና ከተፈቀደው ወንበር በላይ የሚጭኑ አሽከርካሪዎች ላይ ጠንከር ያለ የቁጥጥር ስራ እየሰራ እንደሚገኝ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።

በወልቂጤ ከተማ መናኻሪያ አግኝተን ያነጋገርናቸው መንገደኞች እንደገለጹት፥ በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ምክንያት በማድረግ እየተደረገ ባለው ከታሪፍ በላይ ጭማሪ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እየተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግስት የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት እንዲቀርፍ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅበትና የስምሪት ባለሙያዎችም በተሽከርካሪዎች ላይ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የወልቂጤ ከተማ አሰተዳደር ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽህፈት ቤት ኃለፊ አቶ ትግስቱ ፉጄ እንደገለፁት በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ምክንያት በማድረግ በከተማው ከታሪፍ እና ትርፍ የሚጭኑ አሽከርካሪዎች ላይ ጠንከር ያለ የቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተለይም በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ላይ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ ከዞንና ከሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በጋራ እየተሰራ በመሆኑ በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጦች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

አያይዘውም ህጉን ከመቆጣጠር አንጻር ከመናኸሪያ ጀምሮ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት የተሻለ ለውጥ ቢኖርም አሁንም የሚቀሩ ተግባራት መኖራቸውን አስረድተዋል።

በከተማ እስካሁን በላው ከደንብና ከአሰራር ውጭ የሚሰሩ 311 አሽከርካሪዎች እና ባጀጆች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን የገለፁት አቶ ትግስቱ በዚህም 466ሺ 500 ብር በመቅጣት ለመንግሥት ገቢ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ከመናኻሪያ ውጭ በመጫን ላይ የሚገኙ በርካታ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመው፥ አልፎ አልፎ የሚመጣውን ነዳጅ በፍትሃዊነት እንዲሰራጭ ከሚመለከታቻው አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አመላተዋል።

በከተማው ለባጃጆች የቤንዝል እጥረት እንደሌለ የገለጹት ኃላፊው የባጃጅ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ እንዳያስከፍሉ የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽህፈት ቤት የስምሪት የስራ ሂደት አሰተባባሪ አቶ ዘውዴ አግዛ በበኩላቸው፥ በመናኸሪያ ውስጥ ደንብና መመሪያን ተግባራዊ ባደረገ መልኩ በመርሃ ግብሮች መሠረት አሽከርካሪዎች በቅደም ተከተላቸው ህብረተሰብን በፍትሀዊነት እንዲያገለግሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ዘውዴ አክለውም የነዳጅ እጥረት እያጋጠመ በመሆኑ ህብረተሰቡን ከመጠን በላይ ትርፍ እንዳይከፍል ለአሽከርካሪዎች ነዳጅ በመጣ ቁጥር ቅድሚያ እንዲያገኙ እና አገልግሎት እንዲሰጡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የነዳጅ እጥረትን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ህብረተሰቡን በማንገላታትና ከተተመነው ታርፍ በላይ ለማስከፈል የሚጥሩ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

አቶ ሙልጌታ ፈቀደ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽህፈት ቤት የመንገድ ድህንነት ባለሙያ ሲሆኑ አለም አቀፋዊ ችግሮችን መነሻ በማድረግ የሚታየውን የአሽከርካሪዎች ህገወጥነትን ለመከላከል አጽንኦት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የነዳጅ እጥረትን ተከትሎ ከታሪፍ በላይ እና ትርፍ ሰው የሚጭኑ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር በከተማው በሰባት ቤት ማዞሪያና ጋሶሬ አከባቢዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ሲሉ አመላክተዋል።

በወልቂጤ ከተማ አግኝተን ያነጋገርናቸው አንዳንድ የባጃጅ ሾፌሮች በሰጡት አስተያየት የነዳጅ እጥረት ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ የሚታወቅ ቢሆንም በከተማው አስተዳደር በወጣው መመሪያ መሠረት ህብረተሰቡን በፍትሃዊነት እያገለገሉ እንደሆነ ገልጸዋል።

እንደ አለም አቀፍ ደረጃ የገጠመውን ፈተና ለመሻገር በመደጋገፍ እና በመተሳሰብ አሽከርካሪዎች አላሰፈላጊ ያልሆነውን ገንዝብ መቀበል እንደማይገባቸውም ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን