የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምክር ቤቶች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባቸው የኮንሶ ዞን ህዝብ ምክር ቤት ገለጸ

የኮንሶ ዞን ሽግግር ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ጉባኤውን በካራት ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የኮንሶ ዞን ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ገልገሎ ኦቶማ ጉባኤውን በንግግር ሲከፍቱ፤ እንደ ሀገር ሰላማዊ እና ፍትሃዊ ምርጫ በተካሄደበት እንዲሁም በሰገን ዙሪያ ወረዳ በተፈጠረ አለመግባባት ህዝባዊ ዕርቀ ሰላም የማስፈንና ህዝቡን የማረጋጋት ተግባራት በተከናወነ ማግስት ጉባኤው መካሄዱ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።

በዞኑ ያለውን አብሮነትና መቻቻል በማጠናከር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል።

የዞኑን ሰላምና ጸጥታ ማጎልበት እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ገልገሎ፤ ሰላሙን በይበልጥ ለማረጋገጥ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተቀናጀ አግባብ መመለስ እንደሚገባ በመጥቀስ፤ በዞኑ ያሉ መዋቅሮች ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም አክለው ገልጸዋል።

በ13ኛው መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አጀንዳዎች ይቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የ2018 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጸም፣ የ2019 ዕቅድ፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2018 በጀት አመት አፈጻጸም ሪፖርትና የ2019 ዕቅድ ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፤ የ2019 በጀት ቀርቦ እንደሚፀድቅም ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ ተዋበች ዳዲ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን