የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት መንግስት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የአርባምንጭ ከተማ ሸማቾችና ነጋዴዎች ጠየቁ
የተከሰተው የነዳጅ እጥረት ለትራንስፖርት ታሪፍ መናርና ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት መሆኑም ተጠቁሟል።
ከአርባምንጭ ከተማ ሸማቾች መካከል መ/ት እልልታ ይስሃቅ እና ጡረተኛ አስር አለቃ ታምሩ ካሳዬ የኑሮ ውድነቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ በዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል።
ከግብርና እስከ ፋብሪካ የፍጆታ ዕቃዎች በገበያ ላይ ቢገኙም በተከሰተው የነዳጅ እጥረት ምክንያት የዋጋ ጭማሪው የሕብረተሰቡን የመሸመት አቅም እየጎዳ መሆኑን ጠቁመው መንግስት ገበያውን እንዲያረጋጋ ጠይቀዋል።
ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ምርት በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ መንግስት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አስተያየት ሰጭዎች አክለዋል።
ቀደም ሲል የነበረው የትራንስፖርት ታሪፊ በእጥፍ በመጨመሩ ከግብርና እስከ ፋብሪካ ምርቶች ዋጋው ያልጨመረ ዕቃ ባለመኖሩ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን ከነጋዴዎች መካከል ወ/ሮ ፍሬሕይወት ዓለሙና ቆንጂት ሶጌ አመላክተዋል።
ምርቶችን እጥፍ ታሪፍ ከፍለውና በውድ ዋጋ ገዝተው ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ነጋዴዎቹ፥ ጭማሪው ሸማቹን እያሸሸ በመሆኑ በነዳጅ ድጎማና ቁጥጥር ላይ መንግስት ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መኮንን ጋትሶ እንደገለፁት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ግብረ ኃይል በማቀናጀት አቅደን እየሰራን ቆይተናል ብለዋል።
ይሁን እንጂ በተከሰተው የነዳጅ እጥረት በትራንስፖርት ጫና ምክንያት ምርትን ለማጓጓዝ ነጋዴው ችግር ስላጋጠመው የዋጋ ንረቱ በሕብረተሰቡ ኑሮ ላይ ጫና መፍጠሩን አቶ መኮንን ተናግረዋል።
ችግሩ ከቤንዝን ይልቅ በናፍጣ ላይ በመሆኑ እህል የሚያመጡ ጅምላ ነጋዴዎች፣ ባለሐብቶች፣ አርሶ አደሮችና የጋሞ ልማት ማህበር ወደ ሰንበት ገበያ ምርታቸውን እንዲያስገቡ ነዳጅ የመሙላት ስራ በልዩነት እየተሠራ መሆኑን የመምሪያው ኃላፊ አክለዋል።
የምርት አቅርቦቱ ከሚታየው ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር በቂ ባይሆንም እጥረት እንዳይከሰት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው በሕብረተሰቡ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም በግብረ ኃይል ስምሪት በማድረግ በሕገ ወጥ መንገድ የተደበቀ 3 ሺህ 820 ሊትር ዘይት በመያዝ ለመንግስት ገቢ መደረጉንም አስረድተዋል
ዘጋቢ፡ ፀሐይ ጎበና – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተመራ የኣሪ ዞን ብልጽግና ፓርቲና የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በሰሜን ኣሪ ወረዳ በመገኘት የተለያዩ የመሰረተ ልማት ተግባራትን መረቀ
ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባው የጂንካ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት የተጠርጣሪ ማቆያና የቢሮ ህንጻ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው በተገኙበት በደማቅ ሥነ ስርዓት በይፋ ተመረቀ
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ቢሊዮን 4 መቶ 21 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ