“ኤርሊንግ ሀላንድን አምበል የምናደርገዉ ከሆነ ትልቅ ችግር ዉስጥ እንገባለን” ኤንዞ ማሬስካ
ለአስር ዓመታት ያህል በኢቲሃድ ስታዲየም ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፉት ፔፕ ጓርዲዮላን ተክተው ማንችስተር ሲቲን የተረከቡት ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ፣ ለአዲሱ የውድድር ዘመን የቡድኑን አምበል የመምረጥ ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
ባለፈው የውድድር ዘመን የአንበልነቱን አርማ ያሰረዉ ፖርቹጋላዊው አማካይ በርናርዶ ሲልቫ በዚህ ክረምት ወደ ሪያል ማድሪድ ማመራቱን ተከትሎ፣ አዲሱ አምበል ማን ይሆናል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ይገኛል።
ማሬስካ ከቀናት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኤርሊንግ ሀላንድን አምበል የማድረግ እቅድ እንዳላቸው ተጠይቀው ትኩረት የሳበ ምላሽ ሰጥተዋል።
አሰልጣኙ እንደገለፁት “በሌስተር ሲቲ እና ቼልሲ እያለሁ ቡድናችን ግብ ሲያስቆጥር አምበሉ ደስታውን ከመግለፅ ይልቅ ከአሰልጣኞች ክፍል መመሪያዎችን ለመቀበል ወደ ተጠባባቂ ወንበር የመምጣት ግዴታ ነበረበት” ሲሉ ማሬስካ ህጋቸውን ገልጸዋል።
ማሬስካ አስከትለዉም “ነገር ግን ጎሉን ያስቆጠረው እራሱ አምበሉ ከሆነ ደስታውን መግለፅ ይችላል። አሁን እንግዲህ ኤርሊንግን ሀላንድ አምበል ብናደርገው አስቡት እንግዲህ ጉድ እኮ ነው የሚሆነው! ትልቅ ችግር ውስጥ እንገባለን” ሲሉ በሳቅ ታጅበው ተናግረዋል።
ማሬስካ አክለውም በጨዋታ ወቅት ለሁለት እና ሶስት ደቂቃ ያህልም ቢሆን የታክቲክ ማስተካከያ ለማድረግ ከአንበላቸው ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።
ሀላንድ ባሳለፍነው የ 2025-2026 የውድድር ዘመን በ 52 ጨዋታዎች 38 ግቦችን ማስቆጠሩ የሚታወስ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ ግብ የሚያስቆጥር ተጫዋች አምበል ቢሆንና ሁልጊዜ ደስታውን ለመግለፅ ቢሄድ አሰልጣኙ መመሪያ ለመስጠት እንደሚቸገሩ በቀልድ አነጋገር አስረድተዋል።
ጨዋታን ስለመምራት ያላቸውን እይታ ሲቀጥሉም “የሁለት እና ሶስት ደቂቃ እረፍት ቢሆን እንኳ ሁልጊዜ በጨዋታው ውስጥ የምናስተካክለው ነገር አይጠፋም። አሁን ላይ ሶስት ወይም አራት አምበሎች አሉን፤ አንደኛው ግን ጎድሎብናል። ሮድሪን በተመለከተ ደግሞ ወደፊት የሚሆነውን አብረን የምናየው ይሆናል” ብለዋል።
ስፔን በ2026 የዓለም ዋንጫን ስታነሳ የቡድኑ መሪ የነበረው ሮድሪ፣ የበርናርዶ ሲልቫን ቦታ ለመተካት ቀዳሚ እጩ ቢሆንም፤ ወደ ባርሴሎና ሊዘዋወር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እስካሁን በሁለቱ ክለቦች መካከል ሙሉ ስምምነት ባይደረስም የዝውውር ወሬው እንደቀጠለ ነው።
ማንችስተር ሲቲ አዲሱን የውድድር ዘመን በይፋ የሚጀምረው ነሐሴ 10 ቀን የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ከሆነው አርሰናል ጋር ለኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫ በሚያደርገው ጨዋታ ሲሆን፣ ነሐሴ 17 ቀን ደግሞ የሊጉን የመጀመሪያ ጨዋታ በሜዳው ከበርንማውዝ ጋር ያደርጋል።
ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ
“ኤርሊንግ ሀላንድን አምበል የምናደርገዉ ከሆነ ትልቅ ችግር ዉስጥ እንገባለን” ኤንዞ ማሬስካ

More Stories
ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ጆርጂና ሮድሪጌዝ የጋብቻ ስነ ስርዓታቸውን ፈፀሙ
ሶማሊያዊው ዳኛ ኦማር አርታን የዩኤፋ ሱፐር ካፕን በዋና ዳኝነት በመምራት የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሊሆኑ ነው
አርሰናል ብሩኖ ጊማራኤሽን በይፋ አስፈረመ