የህግ ታራሚዎችን አምራች ዜጋ ለማድረግ የስነ-ልቦና ድጋፍና የክህሎት ማጎልበቻ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸው ተገለጸ

የህግ ታራሚዎችን አምራች ዜጋ ለማድረግ የስነ-ልቦና ድጋፍና የክህሎት ማጎልበቻ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸው ተገለጸ

የህግ ታራሚዎች ካለፈው ስህተታቸው ተምረው በልማት ስራዎች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ ማህበረሰቡ ከጎናቸው ሊቆም እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የወልቂጤ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የ2018 በጀት ዓመት የክረምት በጎ ፈቃድ አካል የሆነው ለማረሚያ ቤት ታራሚዎች የመንፈስ ማጠንከሪያና መጽናኛ የሚሆን የኪነት፣ የሙዚቃ እና ባህላዊ የጥበብ መርሐ-ግብር አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ ማረሚያ ተቋማት የባህል፣ የእውቀትና የጥበብ ስራዎችን በማፍለቅ በኩል በርካታ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

“በጎነት ለኢትዮጵያ” በሚል በየጊዜው ለሚዘጋጀው የኪነት መርሃ-ግብር ምስጋና አቅርበው ታራሚዎች ነገን ተስፋ በማድረግ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

የወልቂጤ ከተማ ምክትል ከንቲባና የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙባሪክ ዘይኑ በመድረኩ ላይ እንዳስገነዘቡት፤ የህግ ታራሚዎች ነገን በማለም በሀገራዊ የልማት ስራዎች ላይ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።

ይህ የኪነት መርሐ-ግብርም ታራሚዎች ከህብረተሰቡ ሳይገለሉ በስነ-ልቦና እንዲታነፁ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

በቀጣይም የኪነ-ጥበብ፣ የጤና እና ሌሎች አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ከታራሚዎች ጎን እንደሚቆሙና በክረምት በጎ ፈቃድ ስራም የጤና ምርመራ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የወልቂጤ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ይርጋ በበኩላቸው፤ ኪነ-ጥበብ ብሄርና ቋንቋ የማይለይ መሆኑን ጠቅሰው መርሀ-ግብሩ በተለይም ጠያቂ ለሌላቸው ታራሚዎች አለኝታነትን ለማሳየትና የስነ-ልቦና ጥንካሬ ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማው የሚታዩ በርካታ የዕደ-ጥበብ ስራዎች የማረሚያ ተቋሙ ውጤቶች መሆናቸውን ያነሱት ኃላፊዋ ማረሚያ ቤቱ የእውቀት፣ የቋንቋ እና የባህል ማሳደጊያ ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ታራሚዎች የዕደ-ጥበብ ስራዎቻቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩና የገበያ ትስስር ችግሮቻቸው እንዲቀረፉ ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ የተለያዩ የጥበብ ስራዎቻቸውን ያቀረቡት ታራሚዎች በሰጡት አስተያየት፤ ዝግጅቱ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

አክለውም በማረሚያ ቤት በነበራቸው ቆይታ ካለፈው ስህተታቸው በመማር ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ሰላማዊና አምራች ዜጋ ለመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡ ዝናሽ ሙሉጌታ – ከወልቂጤ ጣቢያችን