‎የአለም አቀፉን ተለዋዋጭ ሁኔታ በአግባቡ ለይቶ የሀገር ውስጥ ተጋላጭነትን መቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን በትኩረት በመስራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለፁ

‎የአለም አቀፉን ተለዋዋጭ ሁኔታ በአግባቡ ለይቶ የሀገር ውስጥ ተጋላጭነትን መቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን በትኩረት በመስራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለፁ

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማህበራዊ ክላስተር የብልጽግና ፖርቲ አባላት በወቅታዊ ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጂንካ ከተማ መክረዋል።

‎አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ በውይይቱ ማጠቃለያ እንደገለፁት አለምአቀፋዊ ሁኔታዎች በሀገራችን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ውስጥ ያደረሰውን ተፅዕኖ በመረዳት ህዝብን ያሳተፈ የጋራ አረዳድ በመፍጠር ተግዳሮቶችን መሻገር እንደሚገባ ገልፀዋል።

‎በዚህ ልክ አለም አቀፋዊ ችግሮችን ምክንያት በማድረግ በሀገራችንም ሰው ሰራሽ የሆኑ ተገማች ያልሆኑ ተፅዕኖዎችንም በቅንጅት እየለዩ በፍጥነት እያረሙ መስራት ይገባል ብለዋል።

‎አሁን ባለንበት የበይነ መረብ አለም የዲጂታል ቴክኖሎጂውን የሚያፈልቁና እያንዳንዱን ሀገር የሚቆጣጠሩ ሀገራት የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ከአለም አቀፍ ተቋማት በላይ በሆነበት በዚህ ጊዜ፤ የሀገር ውስጥ ተጋላጭነትን መቀነስ የሚያስችሉ የምርታማነት ሥራዎችንና ምክንያታዊ ያለሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን በመከላከል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

‎በወቅታዊው የነዳጅ ችግር ዙሪያም እንደ ክልል ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ እየተመራ ሲሆን ጥቂት ስግብግቦችን ለማረም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

‎በተመሳሳይ ክልላዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ተግዳሮቶችንና አንፃራዊ የክልላችን የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

‎በተቋም ደረጃ በብቃት የመፈፀም አቅምን በማሳደግ መግባባት በመፍጠር ወጪ በመቀነስ የፖርቲና የመንግስት ቅቡልነትን በማረጋገጥ፤ ሆኖ በመገኘት የመደመር እሴቶችን መላበስ እንደሚገባም አቶ አለማየሁ አመላክተዋል።

‎ከተለመደው አካሄድ በመውጣት ይህንን አለም አቀፍ ጫና አባሉና አመራሩ የጋራ አቋም በመያዝና ትግል በማድረግ ሀገርን ማስቀጠል እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጂንካ ማህበራዊ ክላስተር ብልጽግና ፖርቲ ህብረት ሰብሳቢ አቶ ኢሳያስ እንድርያስ በበኩላቸው፤ አለምአቀፋዊና ሀገራዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመገንዘብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናዎችን መመከት የሚያስችል ቁመና ለመፍጠር አባሉና አመራሩ የጋራ ትግል እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

‎በውይይቱም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሃሳብና አሰተያየቶች ተነስተው በመድረኩ መሪዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

‎ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን