የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ የበና ጸማይ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 13/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ የንጹ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የበና ጸማይ ወረዳ አስተዳደር አስታውቀዋል።
የቃቆና ቀያፈር ከተማ ትላልቅ የንጹህ መጠጥ ዋሃ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች 6 የንጹህ መጠጥ ዋሃ ፕሮጀክቶች በቅርቡ ይመረቃሉ ተብሏል።
ውሃ አጠር በሆኑ ቆላማ የአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በጉልህ የሚስተዋል ሲሆን በደቡብ ኦሞ ዞን የበና ጸማይ ወረዳ አንዱ ነው።
በአካባቢው የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ከፊሎቹ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
በቃቆ ክላስተር የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በአካባቢው የውሃ ችግሩን እያቃለለ ስለመሆኑ ነው ያነጋርናቸው የቃቆ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አሳዬ ስዩም የሚገልጹት።
ከተማው እየሰፋ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ዙሪያ ቀበሌያትን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው የቀያፈር ከተማ የውሃ ፕሮጀክት ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ወጥቶ እየተገነባ ሲሆን፥ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ባለመጀመሩ ከችግር እንዳልተላቀቁ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
ይህ በመሆኑም በከተማው ትራንስፖርትን ጨምሮ ለአንድ ጀሪካን እስከ 30 ብር እየከፈሉ መሆኑን ጠቁመው ችግሩ እንዲቃለልላቸው ጠይቀዋል።
አቶ ፍሬው እንዳለ የቃቆ ቀበሌ ስራ አስኪያጅ ከዚህ ቀደም ማህበረሰቡ ከ 5 እስከ 6 ኪሎ ሜትር ርቀት በመጓዝ ለዚያውም ደህንነቱ ያልተጠበቀ ውሃ ይጠቀም እንደነበር ተናግረዋል።
መንግስት ወርልድ ቪዥን ከተሰኘ አጋር ድርጅት ጋር በመተባበር ያስገነባው ፕሮጀክት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ታክሎበት የአካባቢውን የውሃ ችግር መቅረፍ ስለመቻሉ አብራርተዋል።
የበና ጸማይ የወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ገርሾ በበኩላቸው፥ በቆላማ የአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ 6 ያህል ትላልቅ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በአጋር ድርጅቶች ትብብር እየተገነቡ የሚገኙት እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ100 ሚሊዮኖች ብር በላይ የወጣባቸው ሲሆን በቅርቡ ተጠናቀው የሚመለከታቸው አካለት በተገኙበት በቅርቡ ይመረቃሉ ብለዋል።
በቀያፈር ከተማ የሚስተዋለው የውሃ ችግርን ለማቃለል ከ80 ሚሊዮን ብር የወጣበት የውሃ ፕሮጀከት ርክክብ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ በማመላከት ለሚነሳው ቅሬታ ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።
በቅርቡ የሚመረቁ 6 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች 36 በመቶ የነበረውን የውሃ ሽፋን ወደ 44 በመቶ ያደርሱታል ተብሎም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ ከቱሪዝሙ ዘርፍ ባለፉት 9 ወራት 925.6 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
የወረዳውን ዕድገት ለማፋጠን የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ተቋማት ሊፋጠኑ ይገባል