የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በወ/ሮ አዱኛ አዛዥ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደና አፈ-ጉባኤ አለማየሁ ባውዲን ጨምሮ የክልል፣ የዞን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በወ/ሮ አዱኛ አዛዥ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመኖሪያ ቤታቸው በመገኘት ገለጹ።
ወ/ሮ አዱኛ አዛዥ ለመንግስታዊ ስራ ወጥተው በመመለስ ላይ እያሉ ድንገተኛ አደጋ ደርሶባቸው በህክምና ሲረዱ ቆይተው በትናንትናው ዕለት ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ሲሆን የቀብር ስርዓታቸውም በሣውላ ከተማ በወንጌል አማኞች መካነ መቃብር ፈፅሟል።
ወ/ሮ አዱኛ አዛዥ ከአባታቸው ከአቶ አዛዥ አበበ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ወርቅነሽ አይቸው በ1967 ዓ/ም በጋርዶላ ወረዳ በፋሻ ቀበሌ ተወልደው ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በሣውላ ከተማ በቦትሬ ትምህርት ቤት ከ1ኛ-8ኛ ክፍል በሣውላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ9ኛ-12ኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
በቀድሞ በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ከ1983-1985 ዓ/ም በስምጥ ሸለቆ ግንባር ተሰልፈው በሀገር ደማቅ አሻራ አስቀምጠዋል።
ወ/ሮ አዱኛ የጎፋን ባህል ጠንቅቀው በማጥናት በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ በመሳተፍ በውዝዋዜም አካባቢያቸውን በማስተዋወቅ ትልቅ ኃላፊነት በመወጣት ይታወቁ ነበር።
በመንግስት መስሪያ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በሣዉላ ከተማ በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቀጥረው በታማኝነት ያገለገሉ ሲሆን በቀጣይም ወደ በሣውላ ቤቶች ልማት ተዛውረው በባለሙያነት አገልግለው በቀድመው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል መንግስት ወደ ሀዋሳ ተዛውረው በቤቶች ልማት አስተዳደር በከፍተኛ ባለሙያነት መንግስትና ህዝብን በታማኝነት አገልግለዋል።
የትምህርት ደረጃቸው በአካዉንትንግ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ተምረው ያጠናቀቁና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአዲስ መልክ ሲደራጅ ለስኬቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሀገር ባለውለታ ነበሩ።
ባለትዳርና የ4 ሴት ልጆች እናትና 5 የልጅ ልጆች ያዩ እናት የነበሩት ወ/ሮ አዱኛ አዛዥ፥ ህይወታቸው በድንገት እስካለፈችበት ዕለት ድረስ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ በምክትል የቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአስተዳደርና ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ በነበሩበት ወቅት ለመንግስት ስራ በወጡበት በድንገት በተፈጠረ አደጋ መጋቢት 10/2018 ዓ/ም ልክ ከቀኑ 9:00 ሰዓት ላይ ህይወታቸው አልፏል።
በመጨረሻም በወ/ሮ አዱኛ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተው በመግለፅ የአበባ ጉንጉን በክብር በማስቀመጥ የቀብር ስነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት ተፈፅሟል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በረመዳን ወቅት የታየው ትጋትና አንድነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተመላከተ
1ሺህ 447ኛ የኢድ አል ፈጥር በዓል በኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ አሰተዳደር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከበረ
የጌዴኦ ዞን አስተዳደር የጌዴኦን ተፈጥሮአዊና ባህላዊ መልክዓ-ምድር በመንከባከብ፣ አካባቢውን ለቱሪስት መስህብና ለኢኮኖሚ እድገት ለማዋል በትኩረት እየሰራ ነውሀዋሳ፡ መጋቢት 10/2018 (ደሬቴድ)የጌዴኦ ዞን አስተዳደር የጌዴኦን ተፈጥሮአዊና ባህላዊ መልክዓ-ምድር በመንከባከብ፣ አካባቢውን ለቱሪስት መስህብና ለኢኮኖሚ እድገት ለማዋል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡