የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ እንዲያስችል ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

የዞኑ ገቢዎች እንዲሁም ንግድና ገበያ ልማት መምሪያዎች የህገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር፣ ኑሮ ለማረጋጋት እና የታክስ ህግ ተገዥነት ለማረጋገጥ በጋራ ያዘጋጁት የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በመድረኩ ላይ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ እንዲያስችል ገቢዎች እንዲሁም ንግድና ገበያ ልማት መምሪያዎች ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ ሰብስቦ ለልማት ለማዋል እያደረጉት ያለው የተቀናጀ ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ሁሉም የዞኑ የገቢ አማራጮች በመጠቀም ለላቀ ልማት ቅንጅታዊ አሠራሮችን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚነወር ሃያቱ በ2019 በጀት አመት የዞኑ የገቢ አቅም እና የታክስ መሠረት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ በ2018 የነበሩ ክፍተቶች በማረምና ጠንካራ አፈፃፀሞች በማስቀጠል የተያዘው በጀት አመት እቅድ ለማሳካት ባለድርሻ አካለትን ያሳተፈ ውይይት ማድረጋቸውን ሀላፊው ገልጸዋል።

የታክስ ገቢ መንግስት የህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት ለሚነድፋቸው የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ እንደሆነ የገለፁት አቶ ሚነወር በበጀት ዓመቱ በዞኑ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆነ ታክስ፣ ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎትና ከሌሎች የገቢ አርዕስቶች ከ6 ነጥብ 149 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በገቢ አሰበሰብ ወቅት የሚስተዋሉ ችግሮች ለማረም አጽንኦት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ሀላፊው የታክስ ተገዥነትን በማስፈን ፍትሃዊ የግብር ስርአትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ መኩሪያ ተመስገን መምሪያው ህጋዊ የንግድ ስርአትን በመዘርጋት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በበጀት አመቱ ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ የሚጨመሩና የኑኖ ውድነት እንዲባባስ በሚያደርጉ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን የሰንበት ገበያዎችን ለማጠናከር የፋብሪካና የግብርና ምርቶችን በማቅረብ አምራቹ ከሸማቾች ጋር በቀጥታ በማገናኘት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ለቀጣይ ስራቸው ግብዓት የሚሆን ግንዛቤ ማግኘታቸውን በመጥቀስ በዘርፉ የታቀደውን ዕቅድ በተሻለ ውጤታማነት ለማሳካት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በተለይም በየመዋቅራቸው የሚገኘውን ገቢ በተገቢው እየሰበሰቡ አንደሆነ ገልፀው የህግ ተገዥነትን በማረጋገጥ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ልማት ለማሟላትት በቅንጅት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።

ዘጋቢ፡ ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን