ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋፋት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑ ተጠቆመ

ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋፋት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑ ተጠቆመ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም ፀጋዎችን መጠበቅ፣ ማልማትና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስፋፋት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል “ያልተነካ ተፈጥሮና የብዝኃ ባህል” መገኛነቱን እያረጋገጠ እንደሚገኝ የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የክልሉን ሰፊ የቱሪዝም አቅም ለዘርፉ ዕድገት ለማዋል የቱሪዝም መዳረሻዎቹን በ12 ዘርፎች የመለየት ስራ በማከናወን፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ፍሰት ለማሳደግ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኝ ቢሮው በሰጠው መረጃ አመላቷል፡፡

የቱሪዝም ዘርፉን በሳይንሳዊ መንገድ ለመምራት ሰፊ ጥናት መደረጉን የገለጹት በቢሮው የቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ለምለም አስራት፥ የመስህብ ስፍራዎቹን በማልማት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማላቅ የክልሉ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በየወረዳው አንድ የቱሪስት ማረፊያ እንዲያለማ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፥ ማህበረሰብ አቀፍ ሎጆችን የማስፋፋት ስራ ትኩረት እንደተሰጠው ተናገረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተገነቡት እንደ ሀላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ዳና እና ደምቢ ሎጆች በክልሉ ቱሪዝም ላይ አዲስ መነቃቃት መፍጠሩን የገለጹት ዳይሬክተሯ፥ እነዚህ መዳረሻዎች የጎብኚዎችን ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ከመጨመራቸው ባለፈ፣ ክልሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ቱሪዝም በተጨማሪም የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ፥ ይህንን ዕድል ለማስፋፋትም የአከባቢው ነዋሪዎች በአስጎብኚነትና በምርት አቅርቦት እንዲደራጁ እየተደረገ መሆኑን አመላክተው፥ በየዞኑ አስጎብኚ ማህበራት ተቋቁመው ስልጠናና የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የሰው ዘር እና የቡና መገኛ መሆኗን ተከትሎ በከፋ፣ ሸካ እና ቤንች ሼኮ ዞኖች የሚደረጉ የቡና ጉዞዎች እንዲሁም በምዕራብ ኦሞ የሚገኘው ተወዳጁ የ”ጌሻ ቡና” ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ተመላክቷል።

ክልሉን በዲጂታል ሚዲያ የማስተዋወቅና የሆቴሎችን አገልግሎት ጥራት የመቆጣጠር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑም የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፥ ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ እና የባህል ጸጋ ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በዚሁ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ቅድስት ዐቢይ – ከዋካ ጣቢያችን