ክልሉ ፍጹም ሰላምና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ

ክልሉ ፍጹም ሰላምና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 29/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የዘሩትን ሁሉ የሚያበቅል፣ ፍጹም ሰላም የሰፈነበት በመሆኑ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እየሆነ መምጣቱን የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ እና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ።

የካሳቫ ምርትን ለማስፋፋት ከአርሶአደሩ ባለፈ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን የመደገፍ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ በግብርና ሚኒስተር የግብርና ኢንቨስትመንት እና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ አበበ ተናግረዋል።

የካሳቫ ተክል በተለይም ከዚህ ቀደም በአብዛኛው በአርሶ አደሩ በውስን መሬት የሚመረት እና በተለይም የምግብ እጥረት በሚገጥምበት ወቅት ምግብን ተክቶ ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑን ጠቁመው፥ ምርቱ በተለይ በደቡብ እና በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የሚመረት ቢሆንም በተፈለገው መጠን አለመመረቱ ይነገራል።

ካሳቫ በተለይም በአሁኑ ሰአት በተለያየ መልኩ ለምግብነት የሚውል በመሆኑ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱ ተጠቁሟል።

በደቡብ ምእራብ ክልል በቤንች ሸኮ ዞን ምርቱ ከአርሶ አደሩ ባለፈ በግል ባለሀብቱ እየለማ ሲሆን ምርቱን ለማሳደግ እና ምርቱን አቀነባብሮ የገበያ ትስስር ፈጥሮ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኝ ለማስቻል ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪው አቶ ፍቅሬ አማን እንደተናገሩት ክልሉ እንደ አዲስ ከተዋቀረ ጊዜ ጀምሮ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እያደገ መጥቷል ብለዋል።

የአከባቢ ስነምህዳር የዘሩትን ሁሉ የሚያበቅል ከመሆኑም ባሻገር የአከባቢው ሰላም ክልሉን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዳደረገውም አቶ ፍቅሬ ጠቁመው፥ በክልሉ የካሳቫ ተክል በስፋት እየተመረተ እንደሚገኝና አልሚ ባለሀብቱ በዘርፉ መሰማራታቸው የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን በክልሉ የተጀመረውን የካሳቫ ተክል በስፋት የማምረት ሂደት ውጤታማ እንዲሆን የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት እና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ አበበ በበኩላቸው፥ ካሳቫ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ምርቱን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደውጪ ለመላክ በተለይም ከቻይና ጋር ውል ተገብቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርቱ በተለይም በደቡብ እና በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች በስፋት የሚመረት በመሆኑ ምርቱን በማስፋት የገበያ ትስስር በመፍጠር ከአርሶ አደሩ ባለፈ የግል ባለሀብቱ በዘርፉ እንዲሰማራ በማድረግ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

ለዚሁም የግል ባለሀብቱን በፋይናንስ ማገዝም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ዶክተር ኤርሲዶ ሌንዴቦ የኦሞአዲስ አግሪ ፕላትፎርም አክሲዮን ማህበር ምክትል ስራአስኪያጅ፥ የካሳቫ ምርቱን ከማስፋት እና አቀነባብሮ ፕሮሰስ በማድረግ ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ ለማቅረብም 56 ኢንቨስተሮችን በማሳተፍ እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም በደቡብ ምእራብ ክልል ለካሳቫ ምርት ምቹ ስነምህዳር ያለው በመሆኑ ኢንቨስተሩም ፋብሪካ ገንብቶ ምርቱን እንዲያቀርብ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፥ ይህም ሀገሪቱ ካለመችው የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ትኩረት አንጻር ካሳቫ ትልቁን ሚና እንደሚወጣ ተናግረዋል።

የገበያ የማፈላለግ፣ ምርጥ ዘር የማቅረብ እና ፋይናንስ የማመቻቸት ስራ እየሰሩ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ እና የእርሻ እና ሆልቲካልቸር ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ በበኩላቸው፥ ካሳቫ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ ሰብል መሆኑን ጠቁመው፥ በ2015 የምግብ ዋስትና ንቅናቄ ቢያደርጉም በህዝቡ ዘንድ ብዙ ግንዛቤ አለመኖሩ ተናግረዋል።

ክልሉ ኦሞ ተፋሰስ እና ባሮን ተፋሰስን ይዞ ለዚህ ምርት ምቹ መሆኑን ጠቁመው፥ በተለይም በክልሉ ዳውሮ ዞን በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተጀመረው ወደጉረፈርዳ መሻገሩ ጥሩ ለውጥ እንደሆነም አመላክተዋል።

በዚህም አርሶ አደሩን እና ባለሀብቱን በማቆራኘት በክልሉ ታዋቂ ሰብል ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

ካሳቫ በሄክታር 150 ኩንታል የሚሰጠው ምርት መሆኑን የተናገሩት አቶ አሸናፊ በሰርቶ ማሳያ ላይ በመስራት የተገኘውን ውጤት ለአርሶ አደሩ በማሳየት የማስፋት ስራ ይሰራልም ብለዋል።

በቤንች ሸኮ ዞን በጉረፈርዳ ወረዳ ኮመታ ቀበሌ በእርሻ ኢንቨስትመንት ከተሰማሩት ባለሀብቶች መካከል አቶ ንጉሴ ሀብቴ እና አቶ ግርማ ወንድሙ እና እንዲሁም አቶ ዬሐንስ ካሳሁን በበኩላቸው ካሳቫን ከሌሎች ሰብሎች ጎን ለጎን እያለሙ እንደሆነ ተናግረው፥ ምርቱን በማስፋት ፋብሪካ ለማቋቋም እና ምርቱን ወደውጪ ለመላክ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን