የፓርቲው የምርጫ ማኒፌስቶ የትላንት ጉድለቶችን በማከም ዛሬን በሚገባ ተጠቅሞ ነገን በመተለም የህዝቡን ሁለንተናዊ ብልፅግና በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማድረስ መሆኑን የጎፋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ
በዞኑ መሎ ኮዛ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ማስተዋወቂያ መድረክ ተካሂዷል።
የመሎ ኮዛ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አየለ አምዴ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአገራችን የነበሩ ሁለንተናዊ ስብራቶችን ለመጠገን ብልጽግና ፓርቲ በወሰደው እርምጃ መላው ኢትዮጵያውያን ወደ ስኬት ጉዞ እንዲገቡ አድርጓቸዋል ብለዋል።
ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን ለመገንባት በተወሰደው የኢኮኖሚ ሪፎርም የውስጥ ፀጋዎችን የማጉላት አቅሞችን የመለየትና በየደረጃው ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መቻሉን አስረድተዋል።
የዲጂታል አገልግሎቶችን በመስፋፋት ግልፅነትና አገልግሎት አሰጣጥን እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማጠንከር በተወሰዱ ርምጃዎች ፍትህን እና ተጠያቂነትን ማጠናከር እንደተቻለ አንስተዋል።
የምርጫ 2018 ዓ.ም ማኒፌስቶ የቃል ሰነድ ብቻ ሳይሆን የተግባር ካርታ ጭምር ነው ያሉት ኃላፊው፤ የህዝብ እሴቶችን የሚያንጸባርቅና ከእያንዳንዱ ዜጋ ጋር የሚገባ አዲስ ቃል ኪዳን መሆኑን አረጋግጠዋል።
የመሎ ኮዛ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉነህ አውሳቶ በበኩላቸው፤ ፓርቲው በሀገራችን ኢትዮጵያ ሥር የሰደዱና የቆዩ ችግሮችን በመቅረፍ ወደ ብልፅግና ማማ ለመሻገር የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ ይዞ በመጓዝ ላይ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ሀገር ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነታችን እያደገ መምጣት ችሏል ያሉት አስተዳዳሪው፤ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የምስራቅ አፍሪካ ጂኦ ፖለቲካን የቀየረ ታላቅ ስኬት መሆኑን አመላክተዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማደራጀት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ህዝብን የማወያየት ሥራ እንዲሁም በመደመር እሳቤ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማምጣት የሀገረ መንግስት ግንባታ የማካሄድ ሥራዎች ጎልተው የወጡና የለውጡ መንግስት የብልፅግና ጉዞ ስኬት ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቅሠዋል።
በሌማት ትሩፋት የማምረት ስትራቴጂ በርካታ የወተት መንደሮች፣ የንብ መንደሮች፣ የዶሮ መንደሮች፣ የጓሮ አትክልትና የመሳሰሉት ምርቶች መንደሮች በመፈጠራቸው ህብረተሰቡ የምግብ ዋስትናውን ከጓሮው ከማረጋገጡም በላይ የተረፈውን ገበያ በማስገባት የራሱን ኢኮኖሚ እያበለፀገ ይገኛል ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙት የጎፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና የመንግስት ረዳት ተጠሩሪ አቶ ይሁን ደምሴ፤ የፓርቲው የምርጫ ማኒፌስቶ የትላንት ጉድለቶቻችንን እንድናክም፣ ዛሬን በሚገባ እንድንጠቀም እና ነገን እንድንተልም የሚያደርገን ሲሆን ግባችንም የሀገራችን እና የህዝባችን ሁለንተናዊ ብልፅግና በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማድረስ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ባለፉት የብልፅግና ጊዜያት የጎፋ ህዝብ ለአመታት ሲጠይቅ የኖረዉ የመዋቅር ጥያቄ የተመለሰበት፣ 7 መዋቅሮች ወደ12 የተሸጋገሩበትና በእጥፍ ማደግ የጀመሩበት ነዉም ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ሌብነትና ሙስና ከህሊና ቢስነት የሚመነጩ ናቸው ብሎ ስለሚያምን አምርሮ ይታገላቸዋል ያሉት አቶ ይሁን፤ በራሱ መዋቅር ውስጥም ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ የሌብነት አስተሳሰቦችና ተግባራት ሲያጋጥሙ ያለምንም ርህራሄ ተከታትሎ በማረም በእምነት እና ንፅህና የሚኖር ትዉልድ እንዲፈጠር ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በመጨረሻም በመሎ ኮዛ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ ምልክት ማስተዋወቂያ መርሐ ግብር በልዩ ልዩ ሁነቶች ተከናውኗል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የጤና ፕሮግራምና ኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ የተግባር አፈፃፀም ግምገማና የውይይት መድረክ ተካሄደ
ወጣቶች ግጭትን በመከላከል ረገድ ሊኖራቸው የሚገባ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በመመዝገብ የሚፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመርጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ጥሪ አቀረበ