በቀቤና ልዩ ወረዳ የሚገነቡት የኢማም ሀሰን ኡንጀሞ ሆስፒታል እና የፈትሁዲን ላሉተ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች የማህበረሰቡን የዘመናት የልማት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ መሆናቸውን ተገለፀ

በቀቤና ልዩ ወረዳ የሚገነቡት የኢማም ሀሰን ኡንጀሞ ሆስፒታል እና የፈትሁዲን ላሉተ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች የማህበረሰቡን የዘመናት የልማት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ መሆናቸውን ተገለፀ

በአዲስ አበባ በታሪካዊ አድዋ አዳራሽ በተካሄደው ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ የሚውል የገቢ አሰባሰብ መርሃ ግብር ከ150 ሚሊየን ብር በላይ በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታና የቀቤና ልማት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሙአዝ በድሩ እንዳሉት፤ የቀቤና ልማት ማህበር ከምስረታው ጀምሮ የልዩ ወረዳውን ማህበረሰብ የልማት ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

አሁን ላይ ልማት ማህበሩ ከሚተገብራቸው የ5 ዓመት ስትራቴጂክ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የኢማም ሀሰን ኡንጀሞ ሆስፒታል እና የፈትሁዲን ላሉተ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ ያሉት ዶ/ር ሙዓዝ፤ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ለነገው ትውልድ ብሩህ ተስፋና የተሻለ ህይወት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ በይፋ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማህበረሰቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ አበረታች መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ዶ/ር ሙዓዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ አሚን በደዊ በበኩላቸው፤ በልዩ ወረዳው የሚገነቡት የኢማም ሀሰን ኡንጀሞ ሆስፒታል እና የፈትሁዲን ላሉተ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ የማህበረሰቡን የዘመናት የልማት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እንደ ሀገርም ሆነ ማህበረሰብ ያለ ህዝብ ንቁ ተሳትፎ ልማት አይታሰብም ያሉት አቶ መሀመድ አሚን፤ በልዩ ወረዳው በጤና፣ በትምህርትና በሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ መረባረብ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ጤናማና አመራች ዜጋ ለመፍጠር የፕሮጀክቶቹ ሚና የጎላ መሆኑን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው፤ የጀመርናቸውን የልማት ፕሮጀክቶችን አጠናቀን ሌላ ለመጀመር የሚያስችል ህዝባዊ የልማት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በልዩ ወረዳው የሚገነቡት የኢማም ሀሰን ኡንጀሞ ሆስፒታል እና የፈትሁዲን ላሉተ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ለማህበረሰቡ ያላቸው ፋይዳ የጎላ መሆኑን የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም በልማት ማህበሩ ጎን በመሆን ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ በታሪካዊ አድዋ አዳራሽ በተካሄደው ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ የሚውል የገቢ አሰባሰብ መርሃ ግብር ከ150 ሚሊየን ብር በላይ በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉ ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን