በክልሉ አጠቃላይ የትምህርት ጥራት፣ ቁጥጥርና የደረጃ ምዘና የአሰራር ስርዓት ለውጥ እየታየበት መምጣቱ ተገለጸ

በክልሉ አጠቃላይ የትምህርት ጥራት፣ ቁጥጥርና የደረጃ ምዘና የአሰራር ስርዓት ለውጥ እየታየበት መምጣቱ ተገለጸ

ሀዋሳ: የካቲት 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአጠቃላይ የትምህርት ጥራት፣ ቁጥጥርና የደረጃ ምዘና የአሰራር ስርዓት ለውጥ እየታየበት መምጣቱን የክልሉ ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርቱን አድምጧል።

በክልሉ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት፣ ቁጥጥርና የደረጃ ምዘና የአሰራር ስርዓት ለውጥ እየታየበት መምጣቱን የገለፁት የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተርና የምዘና ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስፍን ሲሳይ፥ በስልጠና ተቋማት መደበኛና መደበኛ ባልሆነ ሥልጠና የተለያ የሙያ ባለቤት የሆኑትን ባለሙያዎች በአገር አቀፍ የሙያ ደረጃና ምደባ መሠረት በተዘጋጀ የምዘና መሣሪያ፤ ዕውቅና በተሰጠው ምዘና ጣቢያና መዛኝ ባለሙያ ተጠቅሞ በመመዘን ብቁ ለሆኑት የምስክር ወረቀት በመስጠት ወደ ሥራ ገበያው እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የተቋሙ አደረጃጀት በአድስ መዋቀር ምክንያት መሰረታዊ የሥራ ሂደት (BPR) ጥናት በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመው፥ ISO-17024 አስመልክቶ ከደረጃዎች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር የግብ ስምምነት በመፈራረም ወደ ስራ መገባቱን አመላክተዋል።

በሙያ ደረጃ፣ በምዘና ትግበራ ወይም በመዛኝ፣ በምዘና ማዕከላት/ጣቢያዎችና በሱፐርቪዥን እንዲሁም በአጠቃላይ የሙያ ብቃት ምዘና ዙሪያ የግንዘቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከኢንዱስትሪ ለተወጣጡ አመራሮችና ለከፍተኛ ባለሙያዎች ተሰጥቷል ብለዋል።

የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በቀረበው የእቅድ አፈፃፀም ዙሪያ ግልፅነትና ማብራሪያ በሚሹ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፥ ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል የተሰራው ስራ አበረታች መሆኑን ጠቁመው፥ ሰርተፍኬቶችን በማጣራት ሀሰተኛ መረጃ መለየት መቻሉ፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በ85% መቀነሱ በጠንካራ ጎኑ ተወስዷል።

የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ምዘና ላይ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ካለው ፋይዳ አንፃር ግምት ውስጥ በማስገባት የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባ ተመላክቷል።

የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እመቤት ወንድሙ በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ነጥቦች ልይ በሰጡት አስተያየት፥ የጥራት ቁጥጥርና ክትትል በማጠናከር የትምህርትና ስልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ የኢንስፔክሽንና የቁጥጥር ስራዎችን ይበልጥ ማሳደግና የምዘና ስርዓቱን ዘላቂ ለውጥ የሚያመጣ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በመጠቀም የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን ማዘመንና የምዘና ሂደቱን ይበልጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፥ በዛው ልክ የመዛኞችን አቅም በማሻሻል ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የክልሉን የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጸሐይ ወራሳ፥ በቋሚ ኮሚቴ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ