በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ የተጀመሩ ስራዎች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ
“ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ቃል የእናቶች ወር በቡታጅራ ከተማ ለ20ኛ ጊዜ ተከብሯል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በየአመቱ ጥር ወር የሚከበረው የጤናማ እናትነት ወር ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ “ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ቃል ለ20ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው ብለዋል።
ቀደምሲል በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ እናቶች ቁጥር ከ25 አመት በፊት 871 ከመቶ ሺህ በመሆን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከነበረበ በቅርቡ እ.አ.አ 2026 በተጠና ጥናት 141 ከመቶ ሺህ መቀነሱ በቀጣይ 2030 የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል አቶ ሳሙኤል።
ለዚህም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ትልቁን አስተዋጽኦ ማበርከቱን የተናገሩት የቢሮው ኃላፊ፤ ለዕቅዱ ስኬታማነት የማህበረሰቡን የግንዛቤ ደረጃ ማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወሊድ አፈጻጻም በጤና ተቋማት ጀረጃ ከሌሎች ክልሎች የተሻለ አፈጻጻም ማስመዝገቡንና ለዚህም ማህበረሰቡን ያሳተፈ ስራ መስራት፣ ማጠናከር ብሎም በመንግሥት በኩል የአምቡላንስ አገልግሎትና መሰል አሰራሮችን ማመቻቸት ተገቢ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ ተገኝተው አስተያየት የሰጡት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ልዩ አማካሪ ንጉሴ አስረስ (ዶ/ር)፤ የሚሰጡ የግንዛቤ ስራዎች መረጃ ከመስጠት ባለፋ በተግባር የሚታይ ውጤት ማምጣት ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካለትም የጤናማ እናትን ዕቅድ ለማሳካት አጋዥ የሚሆኑ የጤና አገልግሎት ግብአት አቅርቦት ላይ ትኩረት ማድረግ ብሎም ማህበረሰብን ያሳተፋ አሠራርን መከተል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትልና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸነፊ ጴጥሮስ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ገለጻ፤ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ፈጠራ የታከለበት አሰራርን መከተል ወሳኝ ነው ብለዋል።
ለዚህ አሠራር ተግባራዊነት በክልል ደረጃ የተጀመሩ ስራዎች መኖሩን ጠቁመው በተለይ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ስራ የመጡ ለውጦችን ዘላቂነት ለማስጠበቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ከአምቡላንስ፣ ከደም ባንክና መሰል የጤና አጋዥ ግብአት አቅርቦት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከጤና ሚኒስቴር ጋር ጭምር በመነጋገር ለመፍታት እንደሚሰራ ተጠቁሟል።
በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የልዩ ወረዳዎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በመጨረሻም የቡታጅራ የሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታ ጉብኝት ተደርጓል።
ዘጋቢ: አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ አጠቃላይ የትምህርት ጥራት፣ ቁጥጥርና የደረጃ ምዘና የአሰራር ስርዓት ለውጥ እየታየበት መምጣቱ ተገለጸ
የፃማኮ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ የ”ባርባይሳ” በዓል የህብረ ብሄራዊ አንድነት መገለጫ፣ የሰላምና የመተሳሰብ ምልክትነቱን በማግዘፍ ለዓለም አደባባይ ማብቃት ይገባል ሲሉ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ገለጹ
በ6 ወራት ውስጥ ሊመዘበር የነበረ ከ156 ሚሊየን 560ሺህ ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ