የፃማኮ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ የ”ባርባይሳ” በዓል የህብረ ብሄራዊ አንድነት መገለጫ፣ የሰላምና የመተሳሰብ ምልክትነቱን በማግዘፍ ለዓለም አደባባይ ማብቃት ይገባል ሲሉ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ገለጹ
ይህንን ያሉት የፃማኮ ብሄረሰብ ዘመን መለወጫ የ”ባርባይሳ” በዓል በብራይሌ ከተማ በድምቀት በተከበረበት ወቅት ነው።
ከተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች የተገኙ እንግዶችን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልልና የዞን የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የፃማኮ ብሄር የዘመን መለወጫ የ”ባርባይሳ” በዓል በድምቀት ተከበሯል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የበና ጸማይ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ጋርሾ፤ የ”ባርባይሳ” በዓል ተለምዷዊ ብቻ ሳይሆን ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትን የምንመረምርበት ነገንም የምንተነብይበት የማንነታችን ዓርማ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የበአሉ እሴቶች ሰላምና ፍቅር ይቅርታና አንድነት እንደመሆናቸው ይህንኑ ዕውን ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማልኮ፤ የማንነት መገለጫ የሆነው የ”ባርባይሳ” በዓል በአግባቡ ተሰነዶ ለትውልድ ሊተላለፍ ይገባል ብለዋል።
“ህብረብሄራዊ አንድነት ለብልጽግና” በሚል መርህ መከበሩ ልዩ ትርጉም አለው ያሉ ሲሆን በዓሉን ስናከበርም በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በሌሎችም የልማት መስኮች ውጤታማ ለመሆን የምንነሳበት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የበዓሉ በዓደባባይ መከበር ማህበረሰባዊ እሴትን በዓለም መድረክ ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን በማድረግ ረገድም ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ወላይቴ ቢቶ በበኩላቸው፤ የፃማኮ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ የህብረ ብሄራዊ አንድነት መገለጫ የሰላምና የመተሳሰብ ምልክትነቱን በማግዘፍ ለአለም አደባባይ ማብቃት ይገባል ብለዋል።
ከአባቶቻችን የወረሰነው ባህላዊ እሴት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚጠናከርበት ለሰላምና ልማትም በጋራ የምንተጋበት መሆን ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል።
ከአባቶች ከተወረሱ እንቁ ባህሎች ጥሩዎቹን በማጎልበትና በማዘመን በጥናት ላይ የተመሠረተ ስራ መስራት እንደሚገባም አስምረውበታል።
በተለይም የተማሩ የማህበረሰቡ ተወላጆች እጅ ለእጅ በመያያዝና ከመወቃቀስ በመላቀቅ ለማህበረሰቡ ለውጥ የተቀናጀ ጥረት በማድረግ ለሀገር ብልጽግና መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
4ኛው የ”ባርባይሳ” በዓል በብራይሌ ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ስነ-ስርዓቶች በድምቀት ተስተናግዷል።
ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጅንካ ጣቢያችን

More Stories
በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ የተጀመሩ ስራዎች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ
በ6 ወራት ውስጥ ሊመዘበር የነበረ ከ156 ሚሊየን 560ሺህ ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ
የጉራጌ ክትፎ ባህልና እውቀትን በዩኒስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ ቅርስ ባለስልጣን ገለፀ