“አስቶን ቪላን ብወደውም ዩናይትድ ታላቅ ክለብ ነው” ዩሪ ቲሌማንስ



ቤልጂዬማዊው አማካኝ ዩሪ ቲሌማንስ  በአስቶን ቪላ የነበረውን የ35 ሚሊዮን ፓውንድ የውል ማፍረሻ ክፍያ ተፈፅሞለት በአምስት ዓመት ውል ማንቸስተር ዩናይትድን መቀላቀሉ ይታወቃል።

ተጫዋቹ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ላይ በነበረበት ወቅት የተጠናቀቀውን ይህንን ዝውውር አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚዲያዎች በሰጠው ዝርዝር መግለጫ፣ስለ አዲሱ ጉዞው እና ከዚህ ቀደም ከዩናይትድ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ተናግሯል።

ቲሌማንስ ቀደም ሲል እ.ኤ.አ በ2019 እና በ2022 ማንቸስተር ዩናይትድን ለመቀላቀል ጥረት አድርጎ እንዳልተሳካለት አስታውሶ፣”በሶስተኛው ሙከራ ተሳክቷል” ሲል ደስታውን ገልጿል።

ከቀድሞ ክለቡ አስቶን ቪላ ጋር ስለነበረው ቆይታ ሲናገርምለቪላ ትልቅ ክብር እና ምስጋና አለኝ፤ ወደ ጥንካሬዬ እንድመለስ አድርገውኛል። ነገር ግን ከቪላ በላይ የሆኑ ትልልቅ ክለቦች አሉ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ አንዱ ነው ብሏል።

ቲሌማንስ ከክለቡ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ ጋር ያለው ግንኙነት በፍጥነት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጾ፣ከፒኤስጂ ጋር በነበረው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ሁለቱም ተጫዋቾች ተቀይረው ወደ ሜዳ ከገቡ በኋላ የነበራቸው የአጭር ደቂቃዎች እንቅስቃሴ ጥሩ አመላካች መሆኑን ጠቁሟል።

ገና በ16 ዓመቱ በፕሮፌሽናል ደረጃ መጫወት የጀመረው የ29 ዓመቱ አማካኝ፣ እስካሁን ከ668 በላይ ጨዋታዎችን አድርጓል።

 በቅርቡ በዓለም ዋንጫው ወቅት ከስፔን ጋር ከመጫወታቸው በፊት ያጋጠመው የጡንቻ ጉዳት የጨዋታዎች መደራረብ ያስከተለው እንደሆነና አሁን ግን በሙሉ አካል ብቃት ላይ እንደሚገኝ አረጋግጧል።

በሌስተር ሲቲ አብረዉት የተጫወቱት ጆኒ ኢቫንስ እና ሃሪ ማጉዋየር እንዲሁም በቪላ በውሰት አብሮት የነበረው ማርከስ ራሽፎርድ በኦልድ ትራፎርድ በፍጥነት እንዲለመድ ትልቅ እገዛ እያደረጉለት እንደሚገኙ ተናግሯል።

በሌስተር ሲቲ የ2021 የኤፍኤ ካፕ  እና በቪላ የኢሮፓ ሊግ አሸናፊነት ላይ ወሳኝ ግቦችን ያስቆጠረው ቲሌማንስ፣ አሁንም በኦልድ ትራፎርድ ተጨማሪ ስኬቶችን እና ዋንጫዎችን ማሸነፍ ዋና ዓላማው እንደሆነ ገልጿል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ