የጉራጌ ክትፎ ባህልና እውቀትን በዩኒስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ ቅርስ ባለስልጣን ገለፀ
በጉዳዩ ላይ በተካሄደው ጥናት ዙሪያ በወልቂጤ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለፁት፤ የጉራጌ ህዝብ መገለጫ ከሆኑ በርካታ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል የክትፎ አዘገጃጀትና አመጋገብ ስነ-ስርዓት ከህዝቡ የረጅም ዓመታት ታሪክና የዕለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴ ጋር ትስስር ያለው ነው፡፡
የምክክር መድረኩ ዓላማም ክትፎን በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተዘጋጀውን ሰነድ መገምገምና የማስመረጫ ሰነዱ አካል የሚሆኑትን ፎቶግራፎችና የቪዲዮ ዶክመንታሪ ፊልም ተመልክቶ ሀሳብ መስጠት ነው ብለዋል፡፡
ህዝቡ በተለያዩ ዐውዶች ላይ በሚኖረው መስተጋብር ባህላዊ ክትፎ የመስተንግዶ ቀዳሚው የምግብ ምርጫ ዝግጅት በመሆኑ ለእርስ በርስ የግንኙነት አድማስ መስፋትና ለባህል እድገት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰሩ፡፡
ቅርሱን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ተቋማት የቱሪስት መስህብነቱን ከፍ በማድረግ ሀገሪቱ በኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ሰነዶቹ የጉራጌ ክትፎ አዘገጃጀትና አመጋገብ ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም ሌሎችም ተያያዥ የባህል እሴቶች በአግባቡ የተተረጎሙባቸው መሆናቸውን፣ የማህበረሰቡን ድምጽ፣ እሴቶች እና ልምዶች በመወከል ትክክለኛነቱን፣ ዶክመንተሪ ፊልሞቹን ከባህል እና ከቴክኒክ አንፃር በመገምገም ሀሳቦች እንዲዋጡ ለማስቻል ነው ብለዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ፤ ክትፎ የጉራጌ ብሄረሰብ ከሚታወቅበት ባህላዊ የምግብ አይነት አንዱ ሲሆን ምግቡ ከብሄረተሰቡ አልፎ በመላ ሀገሪቱ እንዲሁም ከሀገር ውጪም በትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊያን የሚያውቁ የሚወዱት የጉራጌ እንስቶች ልዩ የሙያ መገለጫ ነው ብለዋል፡፡
የክትፎ ባህላዊ አዘገጃጀት በውስጡ ብዙ አውድና ሂደት ያለው ሲሆን ከምግብነት ባሻገር የብሄሩን የአመጋገብ፣ የአኗኗር፣ የሥራና ሌሎችም እሴቶች የሚንፀባረቅበት ስለመሆኑ አብራርተዋል አቶ ሳሙኤል።
እንደ ክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ የጉራጌ ባህላዊ የክትፎ አዘገጃጀት በሁሉም የጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ በልዩ ሁኔታ የሚዘወተር ከመሆኑም ባሻገር ለዞኖችም ይሁን ለክልሉ ልዩ መገለጫ እንዲሁም አንዱ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን አየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ የጉራጌ ክትፎ አሰራር ልዩ እውቀትና ጥበብ የሚጠይቅ እና ከዝግጅቱ እስከ አመጋገቡ በብሄሩ ልዩ ጥንቃቄና ትኩረት ተሰጥቶት በክብር የሚዘጋጅ የምግብ አይነት እንደሆነ አብራርተው የጉራጌ ህዝብ ኑሮውን በእንሰት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተከትሎ የእንሰት ውጤት የሆነው ቆጮ እና ክትፎ ደግሞ የማይነጣጠሉ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው ብለዋል።
የጉራጌ ክትፎ ዛሬ ላይ ብሄራዊ ምግብ ከመሆኑም ባሻገር ከምግብ ስያሜነት አልፎ የንግድ ምልክት እየሆነ ይገኛል ያሉት አቶ ላጫ፤ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ የሆነው የጉራጌ ክትፎ ከሀገራችን አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ሀገራችን ኢትዮጵያን እንዲያስጠራ በዩኔስኮ ወካይ ቅርስነት እንዲመዘገብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የኢፌዲሪ ቅርስ ባለስልጣን የጉራጌ ክትፎ ባህልና እውቀትን በዩኒስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት ባካሄደው ጥናት ዙሪያ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ሀሳብ አስተያየት ቀርበው ከቅርስ ባለስልጣንና ባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በ6 ወራት ውስጥ ሊመዘበር የነበረ ከ156 ሚሊየን 560ሺህ ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ
በክልሉ ያሉ ብሔረሰቦችን ባህል ወደፊት በማውጣት የአካባቢውን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ተናገሩ
የጉራጌ ክትፎ ባህልና እውቀትን በዩኒስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ በተካሄደው ጥናት ዙሪያ በወልቂጤ ከተማ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል