በክልሉ ያሉ ብሔረሰቦችን ባህል ወደፊት በማውጣት የአካባቢውን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ተናገሩ

በክልሉ ያሉ ብሔረሰቦችን ባህል ወደፊት በማውጣት የአካባቢውን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ተናገሩ

የዲዚ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ከይ ቢያርግ” የማጠቃለያ ፕሮግራም በምእራብ ኦሞ ዞን በቱም ማጂ ከተማ አስተዳደር ተከብሯል።

የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አስራ ሶስት ነባር ብሔረሰቦች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ ብሔረሰቦች ውስጥ አንዱ የሆነው የዲዚ ብሔረሰብ ነው። ብሔረሰቡ የራሱ ባህልና እሴት ያለው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የዘመን መለወጫ የምስጋና በአል አንዱ ነው።

በአሉ ለሀምሳ አመታት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከብሯል። በበአሉ አከባበር ላይ የተገኙት የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርእሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የዲዚ ብሔረሰብ በርካታ ባህላዊ እሴቶች ያሉት ቢሆንም እነዚህን ወደፊት ከማውጣት አንጻር ሳይሰራ ቆይቷል።

አሁን ከለውጡ በኋላ በርካታ ባህላዊ እሴቶች ወደፊት ማምጣት ተችሏል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ የዲዚ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በአል አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

አካባቢውም እምቅ የማእድን እና ለእርሻ የሚሆን ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት ያለው በመሆኑ ኢንቨስትመንትን በማጠናከር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በአካባቢው ያለው ሰላምን በማስጠበቅ በኩልም ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ፤ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።

ለዚህም ባላባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የአካባቢ ሽማግሌዎች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጸጋዬ ማሞ በበኩላቸው፤ የዲዚ ህዝብ የበርካታ ታሪክ ባለቤት መሆኑን እና በመሀል ወደኋላ የተመለሰ እንደነበር ጠቁመው አሁን እንደአዲስ በመነቃቃት ባህሉን የማስተዋወቅ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአርብቶ አደር ቢሮ ሀላፊ አቶ መቱ አኮ በበኩላቸው፤ ባህላችንን ከዘመናዊው እውቀትጋር በማስተሳሰር ለህዝቦች ብልጽግና የምሁራን ማህበራችንን ሚና ይበልጥ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።

የምእራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታምሩ ቦኒ፤ የመደመር እሳቤን አንግቦ የተነሳው መንግስት እንደእነዚህ ያሉ ድንቅ ባህሎች ተመዝግበው ለቱሪስት መስህብነት እንዲውሉ በአለም እንዲተዋወቁ እያደረገ ይገኛል፡፡ እኛም የሱን ፈለግ ተከትለን ባህሉን የማስተዋወቅ ስራ አጠናክረን እንሰራለን ብለዋል።

የቱም ማጂ ከተማ አስተዳደር አቶ እሸቱ አየለ፤ የቱም ማጂ ከተማ ህዝብ እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ በከተማው መጥተው በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ከተማ አስተዳደሩ በሩን ከፍቶ እንደሚጠብቅ ተናግረዋል።

በአሉ ከፌደራል፣ ከክልልና ከተለያዩ ዞኖች የመጡ የመንግስት ከፍተኛ ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን