ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የጋሞ ዞን ፍትህ መምሪያ በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅበት ተገለጸ

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የጋሞ ዞን ፍትህ መምሪያ በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅበት ተገለጸ

‎የጋሞ ዞን ፍትህ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም እየገመገመ ይገኛል።

‎መምሪያው ለወረዳና ከተማ አስተዳደር ዐቃቢያነ ህጎች በወንጀል መመሪያ ዙሪያ የተዘጋጀ ስልጠና ሰጥቷል።

‎በመርሀ ግብሩ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የጋሞ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ አበዛሽ አይሳሮ፤ ጉባኤው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ለማካሄድ ዝግጅት በምናደርግበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

‎ወ/ሮ አበዛሽ አክለውም፤ የህዝቡን ሰላም በማስጠበቅ አካባቢው የሚታወቅበትን የሰላም እሴት ከማስቀጠል አንፃርም በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ሲሉ ገልፀዋል።

‎የመንግስትን ሀብት ከብክነት መታደግ፣ የሙስናና የታክስ ወንጀሎችን ከመከላከል ባሻገር አምራች ትውልድ እንዲፈጠር በተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰራ ከመሆኑም ባሻገር የህዝብና የመንግስትን ጥቅም የማስከበር ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ኃላፊዋ።

‎የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሪት አለሚቱ ዮሴፍ እንደገለጹት፤ መምሪያው የዞኑን ሰላም ከማስጠበቅና ከማስከበር ባሻገር የህዝብን ጥያቄ በፍጥነት ከመመለስ አንፃር እመርታዎችን አስመዝግቧል።

‎በሴክተር አመኔታን ከመፍጠር አንፃር ጅምር ስራዎች ቢኖሩም እያንዳንዳችን በአስተሳሰብ እና በተግባር ተቃኝተን በቅንጅት መስራት ከቻልን ከህዝቡ የሚነሱ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በፍጥነት እንፈታለን ሲሉም ተናግረዋል።

‎ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ቀጣይ ተግባራትን ከመፈፀም፣ በሙስና የተመዘበሩ የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ከማስመለስ አንፃር በጋራ መረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

‎በመድረኩ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ውስብስብ ወንጀሎች እና የሚያስከትሉትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የጤና ጉዳዮች ዙሪያ አጭር ስልጠና ተሰጥቷል።

‎የመምሪያው የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም የቀረበ ሲሆን በቀረበው ሰነድ ዙሪያ አስተያየትና ጥያቄዎች ተሰንዝረው ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

‎በመርሀ ግብሩ የጋሞ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሪት አለሚቱ ዮሴፍን ጨምሮ የመምሪያው ኃላፊ ወ/ሮ አበዛሽ አይሳሮ ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የአርባምንጭ እና ጨንቻ ማረሚያ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ዐቃቢያነ ህጎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

‎ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን