”ጌዴኦና ሶንጎ”
ደን፣ ቡና እና እንሰት ሕይወቱ የሆነው የጌዴኦ ብሔር የበርካታ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ነው። የጌዴኦ ብሔር መታወቂያ ከሆነው አንዱ ሶንጎ ሲሆን በሶንጎ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ይፈጸማሉ።
ሶንጎ የጌዴኦ የባለ መዋቅር አካል ነው። ሶንጎ የራሱ የሆነ “ሀይቻዎች” አለው። በአንድ ሶንጎ አንድ ዋና “ሀይቻ”ና ምክትል “ሀይቻ” በባለቤትነት ይመሩታል በዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር ታደሰ ክጴ እንደሚናገሩት።
የ”ሶንጎ” ስፍራ የሚመረጠው በብሔሩ ቋንቋ በ”ሐዩዎች” ነው። እነዚህ “ሐዩዎች” ጠንካራ የሥራ ባህልን ጨምሮ ነገር አዋቂዎችና በሁሉም መልካም ተግባራቸው የተመሰከረላቸው ናቸው።
የሶንጎ ስፍራም የሚመረጠው ነዋሪዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መነሻ ነው። የአካባቢው ማህበረሰብ “አሁን እየሰፋን ነው፤ ቁጥራችን ጨምሯል” ብለው ጥያቄ ያቀርባሉ። እነዚህ “ሐዩዎች” ለሶንጎ የሚሆነውን ቦታ ያረጋግጣሉ።
የሶንጎ ቦታን በሚመርጡበት ጊዜ በጌዴኦ ብሔር ቋንቋ “ካዮ(Kaayo)” ይታያል። “ካዮ” የሚያመለክተው መልካም ዕድል(ገድ) መኖር አለመኖሩን ነው። ለአብነት ስለ “ሶንጎ” ቦታ እየተመካከሩ በእንስራ ውሃን የተሸከመች ልጃገረድ ብትመጣ ጥሩ “ካዮ” ተደርጎ ይወሰዳል። ደረቅ ማሰሮ ቢመጣ ግን ቦታው አይሆንም ማለት ነው። ስለዚህ መንፈሳዊ ትርጓሜም አለው።
ቦታው ከተመረጠ በኋላ የአካባቢው ህዝብ ወጥቶ ለባለ ሶንጎው “ሐይቻ” ቤት ይሰሩለታል። በዚህም አካባቢው ሶንጎ ይኖረዋል ማለት ነው።
በአንድ አካባቢ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መሰብሰቢያ ስፍራቸው ነው “ሶንጎ”። ከአባገዳው የሚመጡ መልዕክቶች ወደ ህብረተሰቡ የሚደርሱትም ሆነ ከህብረተሰቡም ወደ አባገዳ የሚደርሱት በ”ሶንጎው በኩል ነው።
በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት፣ ጦርነትና የበሽታ ወረርሽኝ ሲመጣ፣ በብሔሩ ቋንቋ “ማገኖ”ን ለመለመን፣ በቤተሰብና ማህበራዊ ግንኙነት መካከል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሶንጎ ሁነኛ ስፍራ ነው።
የተበደለ ሰው ፍትህ የሚያገኝበት፣ ለማንኛውም ችግሮች መፍትሔ የሚበጅበት ስፍራ ነው የጌዴኦ ሶንጎ። የተበደለ ሰው በሶንጎው መጥቶ ድምጹን ቢያሰማ በዳዩ ግለሰብ በሶንጎው “ሳናቻዎች” ተይዞ ሽማግሌዎች ፊት እንዲቀርብ ይደረጋል፤ ይመከራል፤ ይገሰጻልም።
በሶንጎ መምከርና መገሰጽ ብቻም ሳይሆን አሻፈረኝ የሚል ሲኖር መግረፍ፣ ከፍ ካለም የሞት ቅጣት ፍርድም ይበየንበታል።
የ”ሶንጎ” ቤት ሲሰራ በር አይኖረውም። ምክንያቱም ሶንጎ የሁሉም ነውና። በሶንጎ ከሚካሄደው ባህላዊ ክዋኔ በዘለለ አንድ መንገደኛ በነጻነት ገብቶ ማደር ይችላል። ደጁ ክፍት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው ማህበረሰብ ለመንገደኛው እህልና ውሃ ይቀርብለታል። ለቀጣይ ጉዞው የሚሆነውንም መረጃ ያገኛል። “ሶንጎ” የመረጃ ማዕከልም ነውና።
ታሪክ እንደሚያሳየው ሁሉም የአፍርካ ሀገራት እንደ ሶንጎ አይነት ታሪካዊ የመገናኛ ስፍራ ነበራቸው። በእንዳንድ ተጽዕኖዎች ጠፉ እንጂ ይላሉ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ታደሰ።
ይሁንና የጌዴኦ ብሔር እስካሁን በሶንጎ ይገለገላል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዞኑ ከ7 መቶ በላይ ሶንጎዎች ይገኛሉ። በእነዚህ ሶንጎዎች ፍትሃዊ ዳኝነት ይሰጣል፤ “ማገኖ”ም ይለመናል።
የሶንጎው አስፈላጊነት በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ሶንጎ ለጌዴኦ ሁሉ ነገሩ ነው። አሁን ላይ ላለው ማህበራዊ ቀውስ የሶንጎዎች መላላት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ሶንጎዎችን በመጠበቅና በማልማት ማህበራዊ ቀውሶችን ማቃናት ይቻላል መልዕክታቸው ነው።
የሶንጎዎች ባለቤት የሆነው ጌዴኦ፣ የዘመን መለወጫውን ዳራሮ በዓል እያከበረ ነው። በድጋሚ እንኳን ለ2018 የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ ዳራሮ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
አዘጋጅ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
”ጌዴኦና ሶንጎ”

More Stories
ህግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ፍትህ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት ሥራ አፈፃፀም አደመጠ
ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እንደሚሠራ የዲላ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
በጎፋ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 2 ሺህ 273 መዝገቦች በዐቃቤ ህግ ውሳኔ ማግኘታቸውን የዞኑ ፍትህ መምሪያ አስታወቀ