የእናቶችና ህፃናት ሞት ለመቀነስ እያከናወናቸው የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ውጤት እየተገኘባቸው እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ
የጤናማ እናትነት ወር “ፈጠራ እና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ከተማ ተከብሯል።
የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አየለ ፈቀደ የጤናማ እናትነት ወር ከወትሮ የላቀ የእናቶችና ህፃናት ጤንነት ሊያጎለብቱ የሚችሉ ተግባራት በስፋት የሚከናወኑበት ወር ነው ብለዋል።
አክለውም ተቋማቸው በዘርፍ ከዘጠኙ የትኩረት መስኮች አንዱና ዋነኛው በሆነው የእናቶችና ህፃናት ጤናና ስርአተ ምግብ ማሻሻል ላይ ሰፊ ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል አቶ አየለ።
ከእናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ እስከ ድህረ ወሊድ አገልግሎት በጤና ተቋማት በተገቢው እዲሰጥ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ያብራሩት የመምሪያው ሀላፊ በተለይም እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ያሉ ህፃናት ልየታ በማድረግ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
እነዚህንና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች በጥር ወር ብቻ ተከናውነው የሚያበቁ ሳይሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንቅናቄ ተፈጥሮ የተደራጀና ተከታታይነት ያላቸው ተግባራት እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።
በግማሽ በጀት አመቱ በዞኑ በሀያ የጤና ተቋማት የአልትራሳውንድ እንዲሁም የሲቢሲ ማሽኖች አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል ያሉት አቶ አየለ፤ መድረኩ በቀጣይ ክፍተቶችን በመሙላት ለተገልጋዩ ማህበረሰብ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ሁነኛ ፋይዳ እንደሚኖረው እና በየ ጤና ተቋማቱ የተጠያቂነት ስርአት በመዘርጋ የአገልግሎት አሰጣጡ ይበልጥ እንዲሻሻል የሚያስችል ግብአቶች የተገኘበት እንደነበርም ጠቁመዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል ሜዲካል ዳሬክተር ዶ/ር ተመስገን ወልዴ በበኩላቸው፤ የእናቶች እና የጨቅላ ህፃናት ሞት ለመቀነስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
በሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት ክትትል ለሚያደርጉና ከየጤና ተቋማት ሪፈር ተደርገው የሚመጡ እናቾችን የጤና ችግር መፍትሄ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በመድረኩ አግኝተን ካነጋገርናቸው እስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ እድሪስ አብራር እና አቶ ሽኩር ሸሪፍ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ስርአት በመዘርጋት የእናቶች እና ህፃናትን ህይወት ለመታደግ ሁሉም ማህበረሰብ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።
አክለውም የእናቶች እና የጨቅላ ህፃናት ሞት ለመቀነስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ያሉ ችግሮች በመቅረፍ የእናቶች እና ህፃናትን ህይወት ለመታደግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ማህበረሰብ ተቆርቋሪነትና ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ መሰለች ብርሃኑ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል