በቀረበው የ6 ወራት የመስተዳድር ምክር ቤት እቅድ አፈፃፀም ላይ የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸዉ ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጠ

በቀረበው የ6 ወራት የመስተዳድር ምክር ቤት እቅድ አፈፃፀም ላይ የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸዉ ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጠ

ሀዋሳ: ጥር 25/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ የበጀት አመቱን 6 ወራት የመስተዳድር ምክር ቤት እቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።

የመስተዳድር ምክር ቤቱን ዝርዝር አፈፃፀም ያቀረቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው ናቸው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በጉባዔዉ የመጀመሪያ ቀን ዉሎ ዋና አጀንዳ በሆነዉ የ2018 በጀት የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ላይ ላነሷቸዉ ጥያቄዎች የሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከመንገድና ትራንስፖርት፣ የንጹ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በትምህርት፣ ሰላምና ፀጥታ፣ ኢንቨስትመንትና በሌሎች የልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ ቀርቧል።

በመንገድ ግንባታ፣ ጥገና እንዲሁም ከድልድዮች ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የትራንፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሐመድ ኑርዬ፥ ምንም እንኳ የቀረበው ሪፖርት የ6ወር ቢሆንም፥ የመጀመሪያ ሶስት ወራት የዝግጅት ምዕራፍ በመሆኑ የተግባር አፈፃፀሙ የ3 ወር በሚል ታሳቢ ቢደረግ ብለዋል።

መንገድ ፍላጎትና የተደራሽነት ችግር በሁለም በኩል የሚስተዋል መሆኑን አስረድተው፥ ነገር ግን ከፌደራል መንገዶች አንፃር በቅንጅትና በውይይት እየተሰራ ነው ብለዋል። የፌደራል መንገዶች አስተዳደር ከሚገነባቸው 15 መንገዶች ውስጥ ሁለቱ መጠናቀቃቸውን ጠቁመው ሌሎቹም በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ከንፁህ መጠጥ ውሃ ጋር ተያይዞ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የቢሮ ም/ኃላፊና የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አላይካ ሽኩር፥ በጠንባሮ አካባቢ ፌደራል የቆፈራቸው ጉድጓዶች ዲዛዬኑ በድጋሚ ተሰርቶ የተሰጠበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።

በሃላባ ዞን የሲንቢጣ ውሃ ፕሮጀክት በፌደራል ደረጃ ሀላባ-በሸኖ በሚል የሚታወቅና ግንባታውም እየተከናወነ መሆኑን አመላክተው፥ ነገር ግን ከበጀትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ መዘግየቱን አስረድተዋል።

በመስተዳድር በምክር ቤቱ አፈፃፀም ዙሪያ ሌሎች በገቢ፣ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፥ በነገው እለት በሚኖረው ቆይታ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው ተጨማሪ ምላሽና ምብራሪያ በመሰጠት ቀጠይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ