የዲዚ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የምስጋና በዓል “ከይ ቢያርግ” በምእራብ ኦሞ ዞን በቤሮ ወረዳ እየተከበረ ይገኛል
በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከሚገኙ አስራ ሶስት ነባር ብሔረሰቦች ውስጥ አንዱ የሆነው የዲዚ ብሔረሰብ ሲሆን የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ እንዲሁም የአመጋገብ እና የአለባበስ ሰርአት ያለው ታላቅ ህዝብ ነው።
ብሔረሰቡ በምእራብ ኦሞ ዞን በማጂ እና በቤሮ ወረዳዎች እንዲሁም በቱም ከተማ አስተዳደሮች እና በአጎራባች ወረዳዎች ሰፍሮ ይኖራል።
ብሔረሰቡ በተለይም በማእድን ሀብቱ፣ በሰብል ልማቱ እና በእርባታ የሚታወቅ ቢሆንም ይህንን ባህሉን ወደፊት ከማውጣት አንጻር በሚፈለገው ልክ እንዳልተሰራ ተመላክቷል።
ብሔረሰቡ የራሱ የዘመን አቆጣጠር ስርአት ቢኖረውም ባለፉት ሀምሳ አመታት ተቋርጦ ቆይቷል። ተቋርጦ የነበረውን በማስቀጠል ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ የምስጋና በአል “ከይ ቢያርግ” በመከበር ላይ ይገኛል።
በአሉ በቀበሌዎች ደረጃ ሲከበር ቆይቶ በብሔረሰቡ መገኛ አንዱ በሆነው በቤሮ ወረዳ ጀባ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
በዚሁ የፓናል ውይይት ላይ የተገኙት የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአርብቶ አደር ቢሮ ሀላፊ አቶ መቱ አኮ፤ የዲዚ ብሔረሰብ በታሪክ የራሱ የሆነ ራስ ገዝ አስተዳደር የነበረው ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ አቃፊ ህዝብ ነው ብለዋል።
የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ በአል መከበር ባህልንና የተፈጥሮ ሀብትን በማጥናትና በመሰነድ ለአለም ለማስተዋወቅ እንዲያስችል እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጥላሁን ታደመ በበኩላቸው፤ የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ በአል መከበር የእርስ በእርስ የህዝቦች ትስስርን ያጠናክራል ብለዋል።
የምእራብ ኦሞ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ከበደ ቡርጂ፤ በዞኑ ያሉትን የየብሔረሰቡን እምቅ ባህል የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል ብለዋል።
የዚሁ በአል እንድ አካል የሆነው የዲዚ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በአል አንዱ ነው ያሉት አቶ ከበደ፤ በአሉ የቱሪዝም መሳቢያ የገቢ ማመንጫ እንዲሆን እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በበአሉ ላይ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችም በአሉ መከበሩ ባህላቸው ወደፊት እንዲወጣ እድል እንደፈጠረላቸው ጠቁመዋል።
በቀጣይም ህዝባዊ ለማድረግ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በበአሉ ላይም የክልሉ እና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለአባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ስለብሔረሰቡ አመጣጥ ሶስት ጥናታዊ ጹሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
በትምህርት ሴክተር እየገጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት የትምህርት አመራር ሪፎርም ማድረግ እንደሚያስፈልግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ
በቀረበው የ6 ወራት የመስተዳድር ምክር ቤት እቅድ አፈፃፀም ላይ የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸዉ ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጠ
በ6 ወራት ውስጥ ከ12 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ