‎የ”ዳራሮ” በዓል ከባህላዊ በዓልነት አልፎ ወደ ቱሪዝም ልማት እንዲቀየር ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው – ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር)

‎የ”ዳራሮ” በዓል ከባህላዊ በዓልነት አልፎ ወደ ቱሪዝም ልማት እንዲቀየር ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው – ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር)

‎ሀዋሳ፡ ጥር 25/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የ”ዳራሮ” በዓል ከባህላዊ በዓልነት አልፎ ወደ ቱሪዝም ልማት እንዲቀየር ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ‎የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

‎የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል “ዳራሮ” በዲላ ከተማ አስተዳደር በድምቀት ተከብሯል።
‎
‎የ2018 ዓ.ም ዳራሮ በዓል “ዳራሮ ለባህልና ለቱሪዝም ልማት” በሚል መሪ ቃል ነው በከተማ አስተዳደር ደረጃ በሀሮሬሳ ሶንጎ የተከበረው።
‎
‎የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ(ዶ/ር)፣ የጌዴኦ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠርን ተከትሎ የሚከበረው የዳራሮ በዓል እሴቱን፣ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን የሚያስተሳስርና አንድነትን የሚያጎለብት እንደሆነ ገልጸዋል።
‎
‎በዞን ደረጃ ለሚከበረው የዳራሮ በዓል የዲላ ከተማ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ከንቲባው አመላክተዋል።
‎
‎በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር)፣ የዳራሮ በዓል በዞኑ በሚገኙ በ7 መቶ 25 ሶንጎዎች እየተከበረ መምጣቱን የተናገሩ ሲሆን “ዳራሮ” የሁሉም እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል።
‎
‎ዳራሮ ከባህላዊነት አልፎ ወደ ቱሪዝም ልማት እንዲቀየር ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት አስተዳዳሪው፤ በዳራሮ በዓል ያሉ እሴቶችን በማስተዋወቅ ለቱሪዝም መደላድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
‎
‎ጥር 30/2018 ዓ.ም በዲላ ስታዲየም በሚከበረው የዳራሮ በዓል ከ100 ሺህ በላይ ህዝብ ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ሁሉም በበዓሉ እንዲገኝ ጥሪ ቀርቧል።
‎
‎ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
‎
‎