ባለፉት 6 ወራት ከ1 ነጥብ 1 ቢልየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የተሰበሰበው ገቢም ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው ገቢ ከ620 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አውላቸው ዮሐንስ የ6 ወራት የስራ አፈጻጸምን አስመልክተው በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለሆሳዕና ቅርንጫፍ እንደገለጹት፤ የበጀት ዓመቱ ገቢ መሰብሰብ ከመጀመሩ አስቀድሞ ለግብር ከፋዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት እና የንቅናቄ መድረኮችን በማካሄድ በሐምሌ ወር በይፋ ግብር መሰብሰብ ተጀምሯል።
በተለይ የግብር ስወራና ማጭበርበርን ለማስቀረት በሃይማኖት እና በትምህርት ተቋማት ጠንካራ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ በግብይት ወቅት ለህብረተሰቡ ደረሰኝ የማይሰጡ 90 የንግድ ተቋማት ላይም እያንዳንዳቸው መቶ ሺህ ብር እንዲቀጡ በማድረግ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
ለመንግስት ግብር መክፈል ሲገባቸው ግብር ሳይከፍሉ የቆዩ ከ4 መቶ በላይ የተለያዩ የንግድ ተቋማትን በማሸግ ወደ ግብር ስርዓት እንዲገቡ መደረጉንም አቶ አውላቸው አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት 6 ወራት ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ የገቢ አርዕስቶች 1 ቢሊየን 289 ሚሊየን 449 ሺህ 488 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ቢልየን 148 ሚሊየን 115 ሺህ 533 ብር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው ገቢ በ620 ሚሊዮን 171 ሺህ 586 ብር ብልጫ መኖሩንም ኃላፊው ተናግረዋል።
አዳዲስ የገቢ ምንጮችን መፍጠርና ከዚህ ቀደም በበዓላት ወቅት በተበታተነ መልኩ ይፈጸም የነበረውን የቁም እንስሳትን በበረት ውስጥ ግብይት እንዲፈጸም መደረጉ ለገቢ መጨመር አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አክለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ከ12 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን የገለጹት ኃላፊዉ፤ ባለፉት 6 ወራት በተሰበሰበው ገቢም በከተማው የ24 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ፣ የመንገድ ዳር መብራት እንዲሁም የጎርፍ መውረጃ ቦይ እና ሌሎች ስራዎችም እየተሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ በግብይት ወቅት ደረሰኝ ጠይቆ በመውሰድ እና ግብር ከፋዮችም ተገቢውን ደረሰኝ በመስጠትና ግብርን በወቅቱ በመክፈል ህገወጥነትን መከላከል እንዳለባቸዉና በከተማው የተጀመሩ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ኃላፊው አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለጸ
በአከባቢዉ የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር እጥረት ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው
የአከባቢን እና የሀገርን ሰላም ለማረጋገጥ የሚቻለው ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት ማድረግ ሲቻል መሆኑ ተገለጸ