በከተሞች የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በልዩ ሁኔታ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

በከተሞች የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በልዩ ሁኔታ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ: ጥር 25/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በከተሞች የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በልዩ ሁኔታ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለፁ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

በከተሞች የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በልዩ ሁኔታ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑየጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)፥ በልማት ምክንያት ከቦታቸው የተነሱ 176 የልማት ተነሽዎች ምትክ ቦታ እንዲያገኙ መደረጉን አመላክተዋል።

በመኖሪያ ቤት ህብረት ሥራ ማህበር የተደራጁ 70 የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራትም የግንባታ ቦታ መረከባቸውን ገልፀው፥ ለ2ሺ 245 ሰነድ አልባ ይዞታዎች ሰነድ አግኝተዋል ብለዋል።

የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን በማዘመን በ6 ወራት ውስጥ በ6 ከተሞች ከእጅ ንክኪ የፀዳ አገልግሎትን ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ ሙሉ በሙሉ አገልግሎትን በሲስተም የሚሰጡ ከተሞች ወደ 20 ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፥ እስካሁን 83ሺ 019 ዜጎች ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

የልማትና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ በከተሞች ሌብነትና ብልሹ አሠራርን መታገል በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ያለ ፈቃድ የተያዙ 1ሺ 164 ህገ-ወጥ እና በውላቸው መሰረት ያላለሙ ይዞታዎች ላይ የማስካከያ እርምጃ በመውሰድ በድምሩ 28ሺ 8971 ሄ/ር መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጎ 48 ግለሰቦች ላይ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱ ተመላክቷል፡፡

የከተማ ሥራን ሊያሳልጡ የሚችሉና የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን የሚቀርፉ ልዩ ልዩ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱን ያስረዱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በህብረተሰብ ተሳትፎ 627 ሚሊየን 354ሺህ 486 ብር ከዕቅድ በላይ በማሰባሰብ ለከተማ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ማዋል መቻሉን ተናግረዋል።

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን እንደ ዕድል በመጠቀም በርካታ የከተማ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ያስረዱት ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው፥ ከነዚህ መካከልም የሆሳዕና እና ወልቂጤ ስታዲየም እድሳት፣ የወልቂጤ የአደባባይ እንሰት መለያ ተከላ፣ በሆሳዕና፣ ቡታጅራ፣ ወልቂጤ እና ወራቤ ከተሞች የተገነቡ የአስፋልትና ኮሪደር ልማት ሥራዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

በከተሞች ኮሪደር ልማት ረገድ መሰረታዊ የሆኑ የአስፋልት፣ የሳይክል፣ እና የእግረኛ መንገድ፣ እንዲሁም የመንገድ ዳር አረንጓዴ ልማትና የወንዝ ዳርቻ መናፈሻና መዝናኛ 82 ኪ.ሜ በግንባታ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ 47 ነጥብ 44 ኪ.ሜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

በአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት ከተጀመሩ ሰዉ ተኮር 90 ፕሮጀክቶች ውስጥ በዚህ ግማሽ ዓመት 35 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ለምክር ቤቱ በሪፖርት የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ይህም የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ቁጥርን 84 የሚያደርሰው አፈፃፀም መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ