የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ መንግሥት ወቅቱን የጠበቀና ጥራት ያለው ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያስችል መሆኑን በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የአርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለፀ
ለ10 ተከታታይ ቀናት በአርባምንጭ ማዕከል ሲሰጥ የቆየው ሁለተኛው ምዕራፍ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ስልጠና ተጠናቋል፡፡
ለበርካታ ዓመታት ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን በመሰብሰብ ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የአርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስሜ አንበሴ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሥነ ህዝብና ጤና ጥናት፣ የግብርና ቆጠራ፣ ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናትና የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የትኩረት ዘርፎቹ እንደነበሩም አቶ ስሜ አብራርተዋል፡፡
ቆጠራው ጥቃቅንና አነስተኛ፣ መካከለኛ፣ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እና የንግድ ባህሪ ባላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
የኢኮኖሚ ተቋማት ቆጠራ በሁሉም ከተሞች ቤት ለቤት በመዞርና በገጠር ናሙና በመውሰድ እንደሚከናወን የተናገሩት ኃላፊው፤ የንግዱ ማህበረሰብ በቆጠራ ሒደቱ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአርባምንጭ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኮንን ጋትሶ በበኩላቸው፤ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ መንግስት ጥራት ያለውና መረጃን መሰረት ያደረገ ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያስችለው በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ ለመረጃ ሰብሳቢ ሰራተኞች ትክክለኛ መረጃን በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
መንግስት ፍትሃዊና ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጥ፣ ሀገራዊው ዕድገትን ለመተንበይና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ቆጠራዉ የላቀ ሚና አለዉ ብለዋል፡፡
በአርባምንጭ ማዕከል ለ10 ቀናት በተሰጠው ስልጠና ከስምንት ዞኖች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 300 በላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ከሰልጣኞች መካከል አቶ አማኑኤል አረጋና ወይዘሪት አማረች ደባልቄ፤ ስልጠናው ተጨባጭና ተአማኒ መረጃን እንድንሰበሰብ የሚረዳ ነው ብለው መረጃውን በሚሰበስቡበት ወቅት የማህበረሰቡ ትብብር እንዳይለያቸው ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ መንግሥት ወቅቱን የጠበቀና ጥራት ያለው ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያስችል መሆኑን በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የአርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለፀ

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል