የጎርፍ መውረጃ ቦይ አለመሠራት በቤት ንብረታቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በከምባታ ዞን የዳምቦያ ከተማ አስተዳደር የ02 ቀበሌ ነዋሪዎች ገለጹ

የጎርፍ መውረጃ ቦይ አለመሠራት በቤት ንብረታቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በከምባታ ዞን የዳምቦያ ከተማ አስተዳደር የ02 ቀበሌ ነዋሪዎች ገለጹ

ሀዋሳ፡ ጥር 24/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጎርፍ መውረጃ ቦይ አለመሠራት በቤት ንብረታቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በከምባታ ዞን የዳምቦያ ከተማ አስተዳደር የ02 ቀበሌ ነዋሪዎች በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለሆሳዕና ኤፍ.ኤም ሬድዮ ጣቢያ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

የዳምቦ ከተማ ማዘጋጀ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽ/ቤት በበኩሉ የነዋሪዎቹ ቅሬታ ተገቢ መሆኑን በመጥቀስ ለችግሩም ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ይሰራል ብሏል።

በከተማው ያነጋገርናቸው አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ከዚህ ቀደም የተጀመሩ የተለያዩ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት መሠረት ባደረገ መልኩ መሰራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የከተማው የመሬት አቀማመጥ ለጎርፍ ተጋላጭ በመሆኑና የውሃ መውረጃ ቦይ ሲሰራ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ታሳቢ ያላደረገ በመሆኑ የ02 ቀበሌ ነዋሪዎች በተለይ በክረምት ወቅት ለጎርፍ አደጋ እንደሚጋለጡ ጠቁመው ችግሩ እንዲቀረፍላቸዉ ጠይቀዋል።

ችግሩን ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን የተናገሩት የአካበቢው ነዋሪዎች እስከአሁን ምለሽ አለመግኘታቸውን ተናግረዋል።

የዝናብ ወቅት ሳይመጣ የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መፍትሔ መስጠት እንደሚገባም ነዋሪዎቹ አንስተዋል።

የጎርፍ መውረጃው መንገድ እያስከተለ ያለው ሌለኛው ችግር በከተማ ዙሪያ ያሉ የገጠር ቀበሌያት አርሶ አደሮች የተለያዩ የግብርና ምርቶቻቸውን ለገበያ እንዳያቃርቡ ተፅዕኖ ከማሳዳሩም በላይ ዕለት ተዕለት የሚያደርጉትን እንቅስቀሴ እየገደበ እንደሆነም አክለዋል።

ኢንጂነር ምስጋና ማቴዎስ የዳምቦያ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽ/ቤት ኃላፊ ሲሆኑ ከተማውን ለኑሮ ምቹና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የተለያዩ ዕቅዶች ተይዘዉ ወደ ትግበራ ለመግባት ቅድመ ሁኔታዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

የመምህራንና የቀድሞ ሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በማህበር ተደራጅተው ቤት የሰሩበት አካበቢ ለጎርፍ ተጋላጭ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከችግሩ ስፋት አንፃር ተጨማሪ በጀት ስለሚጠይቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብም የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

የከተማው የመሬት አቀማመጥ ለጎርፍ ተጋላጭ መሆኑን ተከትሎ አብዛኞቹ አካባቢዎች የጎርፍ መውረጃ መንገድ መሠራቱንና አሁንም እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት የከተማው ከንቲባ አቶ አበበ ኤርጊቾ፤ ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንፃር በርካታ ያልተሠሩ ስራዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

ለነዋሪዎቹ ቅሬታ በጊዜያዊነት እና በዘላቂነት ምላሽ ለመሰጠት እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ዘጋቢ: አለማየሁ ማተቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን