የተፈጥሮ ሀብቶች የግጭት መንስኤ መሆን እንደሌለባቸው ተገለፀ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ፍላጎትና ተጓዳኝ ችግሮች ዙሪያ በተደረገ የጥናት ግኝት ላይ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
የተፈጥሮ ሀብታችን ለሰላማችን ግበዓት ነው በሚል ሀሳብ በደቡብ ኦሞ ዞን በሀመርና ዳሰነች ማህበረሰብ ዘንድ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም በሚከሰቱ ግጭቶች ዙሪያ የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከማህበረሰቡ ከተውጣጡ አርብቶ አደሮች፣ ከዞንና ወረዳ ከመጡ አመራሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ምክክር ውይይት ተደርጓል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ሠላምና ፀጥታ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የፀጥታ መረጃና ግጭት መከላከልና አፈታት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መንግስቱ ማጃ፤ የተፈጥሮ ሀብቶች የግጭት መንስኤ መሆን እንደሌለባቸው ገልፀው ያሉንን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በማልማትና በመጠቀም ሰላምን መገንባትና ማፅናት ይገባል ብለዋል።
አክለውም ጥናቱ አሁን ላይ በሁለቱ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ዘንድ ይካሄድ እንጂ በደቡብ ኦሞ ዞን ያሉ አርብቶ አደሮች ዘንድ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ተመሳሳይ ግጭቶች ስለሚከሰት ጥናቱ ቀጣይነት ይኖረዋል ብለው፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ከግጭት ተላቆ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የሰላም ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የግጭት አፈታት ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ወንድማገኝ ማራ፤ የጥናቱ ዋና አላማ የሐመርና ዳሰነች አርብቶ አደር ወረዳዎች ወሰን አካባቢ የሚከሰተውን ግጭት መንስኤ፣ አባባሽ ምክንያቶችና ተዋናዮች፣ የግጭት ጉዳትና ሰለባ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመለየት ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት እና የሠላም ግንባታ አማራጮች ላይ የመንግስትና የባለድርሻ አካላትን ሚና ለማመላከት የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የግንኙነት እድገት ተጠናክሮ ግጭት በዘላቂነት የሚፈታበትን አማራጭ ለመግለፅ ታስቦ ነው ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የግንዛቤ ማሳደግና የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ሀይሌ፤ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ የሚስተዋሉ ግጭቶችን በማስወገድ ሰላምን ለማፅናትና በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ማስወገድ ላይ ወጣቶችና ሴቶችን በማሳተፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አባዱባ ሁና በበኩላቸው፤ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ በአርብቶ አደሩ አካባቢ በሚስተዋሉ ግጭቶችን በዘላቂነት እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ጥናት ማድረጉ የሚበረታታ ነው ብለው በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ የሚከሰቱ ግጭቶች እንደ ሐመርና ዳሰነች ሁሉ በሌሎች አርብቶ አደር አካባቢዎች ስለሚከሰቱ ግጭትን በማስወገድ ሰላምን ለማፅናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የሐመር ወረዳ የምርሻ ኩልማ ቀበሌ የጎሳ መሪ አርብቶ አደር ሰንበሌ ገሌና የዳሰነች ወረዳ የጉሬ ናራማ ቀበሌ አርብቶ አደር ተግጆ ኘማዮ በጋራ በአካባቢያቸው ለከብቶች የግጦሽ ሳርና ውሃ ፍለጋ ሲባል ግጭቶች እንደሚከሰቱና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንደሚደርስ ተናግረው ከጥናቱ ባገኙት ግንዛቤ መሰረት ከአካባቢው ማህረሰብ ጋር በመወያየት ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን በጋራ በመጠቀም በሰላም አብሮ ለመኖር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል