አንትሮሽት የእናቶች የምስጋና በዓል ለትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

አንትሮሽት የእናቶች የምስጋና በዓል ለትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጉራጌ ብሄረሰብ ባህላዊ እሴት መገለጫ አንትሮሽት የእናቶች የምስጋና በዓል ሳይበረዝ በተገቢው መንገድ ለትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ አሳሰቡ።

“አንትሮሽት” ወይም የእናቶች የምስጋና አመታዊ ክብረ በዓል የማጠቃለያ መርሃ ግብር በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በአምበልታ ቀበሌ በድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እናትን ማክበር የጉራጌ ብሄረሰብ ልዩ መገለጫ ባህሉ ነው ያሉ ሲሆን ባህል ደግሞ የአንድ ማህበረሰብ ሁለንተናዊ መገለጫ ነው ብለዋል።

የጉራጌ ብሔረሰብ ከሰለጠኑ የአለም ሃገራት አስቀድሞ የእናት ውለታን በመረዳት፥ እናት መከበርና መመስገን አለባት በሚል እሳቤ አንትሮሽት ወይም የእናቶች የምስጋና ቀን በማለት ማክበር የጀመረ ማህበረሰብ መሆኑን ተናግረዋል።

የጉራጌ ብሔረሰብ ውብ ባህላዊ እሴት መገለጫ የሆነው አንትሮሽት ወይም የእናቶች የምስጋና በዓል እንዳይበረዝ በተገቢው መንገድ ለትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ዘቢባ መሃመድ ናስር የአንትሮሽት በአልን የጉራጌ ብሄረሰብ በ14ተኛው ክፍለ ዘመን ማክበር መጀመሩ በስልጣኔ የቀደመ ማህበረሰብ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

አንትሮሽት በማህበረሰቡ ውስጥ ለበርካታ ዘመን የኖረ የመከባበር ፣ የመተባበር፣ የሰላም እና መሰል እሴቶች እንዲጎለብቱ የሴቶች መብት እንዲከበር እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የሚያስችል መልካም እሴት ሆኖ መቆየቱንም ገልጸዋል።

አንትሮሽት ሴቶች መብታቸው እንዲከበር ድካማቸውንና ጥረታቸው እንዲሁም ልፋቶቻቸው ወንዶች እንዲያውቁት እና እንዲረዱት በጥበብና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የጠየቁበትና ያስከበሩት ውብ ባህል ነውም ብለዋል ወይዘሮ ዘቢባ።

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ነጅምያ መሃሙድ አንትሮሽት የእናቶች ቀን በአል በጉራጌ መከበር የጀመረው በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው ማርች 8 የሴቶች ቀን ከመከበሩ አስቀድሞ የጉራጌ እናቶች ሴቶች ከወንዶች እኩል መብት የጠየቁበት እና ያወጁበት በአላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የቀደሙ እናቶች በቅርስነት አስቀምጠውልን ያለፉትን አኩሪ ባህላዊ እሴት በመጤ ባህል ሳይበረዝ ጥንታዊ ውበቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በጉራጌ ዞን የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሱ ጁሀር የጉራጌ ብሔረሰብ የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ነው ያሉ ሲሆን በዘመናት ካዳበርናቸው አኩሪ እሴቶች መካከል በየአመቱ የሚከበረው የእናቶች የምስጋና በአል አንዱ ነው።

በዚህ እለት እናቶች በቤተሰባቸው በጎረቤቶቻቸው እና በማህበረሰቡ ዘንድ በአጠቃላይ አክብሮት ምስጋናና አድናቆት የሚቸራቸው እለት መሆኑን አውስተዋል።

የክብረ በዓሉ ተሳታፊ እናቶች በሰጡት አስተያየት አንትሮሽት የቀደመ የጉራጌ ባህላዊ እሴት እንደሆነ ገልጸው፥ እናት ባሳደገቻቸው ልጆቿ ስትከበር እና ተገቢውን ትኩረት ስታገኝ በማየታቸው መደሰታቸውን አስረድተዋል።

ይህም ከልጆቻችን ከብርና ምስጋና የምንቸርበት በልጆቻችን የምናርፍበት የደስታ በዓላችን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የ“አንትሮሽት” ወይም የእናቶች አመታዊ በዓል በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ሲከበር የቆየ ሲሆን በዛሬው ዕለት በአበሽጌ ወረዳ የማጠቃለያ መርሃ ግብሩ በማድረግ በቀጣይ የአንትሮሽት በአል እንደጋኝ ወረዳ የሚከበር መሆኑም ተገልጿል።

ዘጋቢ፡ አስቻለው አማረ – ከወልቂጤ ጣቢያችን