አካል ጉዳተኝነት ውጤታማ ከመሆን ያልገደባቸው አቶ ሀብታሙ ለማ
አቶ ሀብታሙ ለማ ይባላሉ። ነዋሪነታቸው በዲላ ከተማ አስተዳደር ኦዳያኣ ቀበሌ ሲሆን ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ናቸው።
አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን መሞከር የሚወዱት አቶ ሀብታሙ የአካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ይረዳቸው ዘንድ በሞተር ሳይክል ላይ ባደረጉት የፈጠራ ሥራ ለመሸለም በቅተዋል።
ተገቢውን ድጋፍ ያጣው የፈጠራ ችሎታቸው ረዥም ርቀት እንደማይዘልቅ የተረዱት አቶ ሀብታሙ ፊታቸውን ወደ ግብርና በማዞር ዕጣ ፈንታቸውን ለመሞከር ቆርጠው ተነሱ።
አቶ ሀብታሙ ከወላጆቹ በድርሻቸው በተሰጣቸው ግማሽ ሄክታር መሬት በቤተሰብ ተደራጅተው የተለያዩ ቋሚ ሰብሎችና እርባታን እያከናወኑ ይገኛሉ።
አቶ ሀብታሙ በአሁኑ ወቅት የግል መኖሪያ ቤት ከመገንባት አልፈው የኪራይ ቤቶችን ገንብተው ተጨማሪ ገቢ ከማግኘታቸው ጎን ለጎን የቤት ፈላጊዎችን ችግር ለመቅረፍ የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
በግብርናው ዘርፍ በስፋት እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት እኚህ ጠንካራ ግለሰብ 3 ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ ቋሚ እና ወቅታዊ ሰብሎችን በኮንትራት እያለሙ ይገኛሉ።
ከዚህ በተጨማሪ በጎችን በማሞከት፣ ወይፈኖችን በማደለብና በሙዝ ምርትም ላይ በስፋት የተሰማሩት አቶ ሀብታሙ በዚህም ውጤታማ ናቸው።
አካል ጉዳተኛነት ያልገደባቸው አቶ ሀብታሙ እስከአሁን ባደረጉት የግል ጥረት ያፈሩት ጥሪት በገንዘብ ቢሰላ ወደ 10 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ነው የገለጹት።
አካል ጉዳተኝነት የአለመቻል መገለጫ አለመሆኑን በጽኑ እንደሚያምኑ ነው ያስረዱት።
የሰውን እጅ መጠበቅ እንደሚጎዳ የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ በአካል ጉዳተኝነታቸው ሳቢያ በነጻነት ተንቀሳቅሰው አገልግሎት ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበርና አንዳንድ አገልግሎት መስጫ አካባቢዎች ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ወ/ሮ ሠራዊት ዳና አካል ጉዳተኝነት ያልበገራቸው ባሌቤታቸው አቶ ሀብታሙ፤ ለጉዳቱ እጅ ሳይሰጡ እንደማንኛውም ሰው ሠርተው ቤታቸውን የሚያስተዳድሩ ትሁት ሰው ስለመሆናቸው መስክረዋል።
አቶ ሀብታሙ ተጨማሪ ድጋፍ የሚያደርግ አካል ቢኖር በርካታ የፈጠራ ተሰጥኦዎች እንዳላቸው ነው ወ/ሮ ሠራዊት የተናገሩት።
የመንግሥት ሠራተኛ መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮዋ፤ በትርፍ ጊዜአቸው ከባለቤታቸው ጎን መሆናቸውን እና ወደፊትም በአስፈላጊው ሁሉ አብረው እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
አቶ ግዛው ወርቁ በዲላ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ የእርባታ ባለሙያ ናቸው። ከእርባታው ዘርፍ አንዱ የዓሣ ሀብት ሲሆን አቶ ሀብታሙ ባቀረቡት ፍላጎት መሠረት በ1 መቶ 20 ካሬ መሬት ላይ ሁለት ኩሬዎች የዓሣ ጫጩቶችን በማስገባት በሙያ እንደሚደግፉና የተሰጣቸውን ግንዛቤ ተግባራዊ የሚያደርጉ ብርቱ ሰው እንደሆኑ ነው የገልጹት።
አዘጋጅ፡ ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
አካል ጉዳተኝነት ውጤታማ ከመሆን ያልገደባቸው አቶ ሀብታሙ ለማ

More Stories
የፈተና አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመን ኩረጃን በማስቀረት የተሻሉ ተማሪዎችን ማፍራት እየተቻለ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የዘንድሮ 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በሀገራችን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት እያደገ መምጣቱን አሳይቷል – የዩኒቨርሲቲ ምሁራን
ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ