የፈተና አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመን ኩረጃን በማስቀረት የተሻሉ ተማሪዎችን ማፍራት እየተቻለ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፈተና አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመን ኩረጃን በማስቀረት የተሻሉ ተማሪዎችን ማፍራት እየተቻለ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
“የዘመነ ፈተና አስተዳደር ስርዓት፣ ለላቀ የትምህርት ጥራት!” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የ2018 ዓ.ም ሀገራዊና ክልላዊ ፈተና አስተዳደር ምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የትምህርት ዘርፍ ልማት ውጤታማነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል የባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ እየተሠራ ይገኛል።
በዚህ ቅንጅታዊ ሥራ የፈተና አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመን ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱንም ገልጸዋል።
አሁን ላይ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ቁሳቁስ በማገዝና ለተማሪዎች ማጠናከሪያ ትምህርት በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነም ተናግረዋል።
የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማደግ አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮቹን ለመፍታት ያስችላልም ብለዋል።
የፈተና አስተዳደር ሥርዓት ለማዘመን የተጀመረውን ተግባር በቶሎ በመላመድ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።
የፈተና አስተዳደር ግብረ ኃይልም በቀጣይ ከኩረጃ የጸዳ የፈተና አሰጣጥ ሁኔታን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው፤ ካለፉት ዓመታት ይልቅ በትምህርት ዘርፍ መሻሻሎች እንዲኖሩ ለማስቻል በተቀናጀ ርብርብ እየተሠራ የሚገኘውን ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።
በፈተና አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ አልፎ አልፎ የሚታዩ ክፍተቶች ሊታረሙ እንደሚገባም የዘርፉ አመራር በኃላፊነት ተቀብሎ ሊሠራ ይገባልም ብለዋል።
የፈተና አስተዳደር ግብረ ኃይል ከፈተና አሰጣጥ ሂደት ጋር ተያይዘው የሚሠሩ ሥራዎችን በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
በውይይቱ የተሳተፉ የትምህርት አመራሮች በሰጡት አስተያየት እንዳሉት፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በየደረጃው የሚገኙ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል ካለፉት ጊዜያት ይልቅ አሁን እየተሻሻለ መጥቷል።
በበይነ መረብ ለሚፈተኑ ተማሪዎች በቂ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።
ይህንን ተሳትፎ በማጠናከር ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ርዕሰ መስተዳደሩ በሰጡት የሥራ መመሪያ፤ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በበይነ መረብ ተማሪዎች መፈተን ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ኩረጃ የማስቀረት ተግባር ላይ ተጨባጭ ውጤት እየታየ ይገኛል።
በመሆኑም የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል በቀሪ ጊዜያት የባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ለዘመነ ፈተና አሰጣጥ ሂደት ተግዳሮት የሚሆኑ ችግሮች ከወዲሁ ተለይተው አጽንኦት ተሰጥቶ እንዲሠሩም ገልጸዋል።
የ2018 ዓ.ም ሀገራዊና ክልላዊ ፈተና አሰጣጥ በተሻለ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከቦንጋ ማስተባበሪያ

More Stories
የዘንድሮ 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በሀገራችን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት እያደገ መምጣቱን አሳይቷል – የዩኒቨርሲቲ ምሁራን
ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
በክልሉ የተጀመረውን የልማት እና መልካም አስተዳደር ሥራዎችን በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከግጭት የጸዳ አካባቢ ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላም እና ፀጥታ ቢሮ አሳሰበ