የዘንድሮ 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በሀገራችን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት እያደገ መምጣቱን አሳይቷል – የዩኒቨርሲቲ ምሁራን

የዘንድሮ 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በሀገራችን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት እያደገ መምጣቱን አሳይቷል – የዩኒቨርሲቲ ምሁራን

የዘንድሮ 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በሀገራችን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት እያደገ መምጣቱን ማሳያ እንደነበር የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡

ምሁራኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመረጣቸውን ህዝብ ድምጽ ሊያከብሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እለተ ሰኞ ግንቦት 24 ተካሂዷል። ምርጫውን አስመልክተው ሀሳባቸውን የሰጡ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን መካከል የታሪክ ቅርስ አስተዳደር መምህር አማረ ፋንታው እና የማህበራዊ ሳይንስ መምህር ሙልቀን አየለ እንዲሁም የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር መለስ ቸኮል፤ ሀገራችን በየአምስት አመቱ ምርጫ እያካሄደች መምጣቷ ጥሩ ተግባር እንደሆነ አንስተዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎአቸው ያደገበት፣ ከ50 ሚሊየን በላይ መራጮች ለመምረጥ የተመዘገቡበት፣ የአትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ቢሆን ተገቢ ዝግጅት ማድረጉ እና ለምርጫ አስፈጻሚዎች ተገቢ የሆነ ስልጠና መስጠቱ እንዲሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለህዝቡ ማሳወቃቸው ጥሩ ተግባር እንደነበር አውስተዋል።

ምሁራኑ በምርጫው እለትም ህዝቡ ከማለዳው እስከ እኩለ ለሊት ድምጽ ለመስጠት መውጣቱ በምርጫው ለመሳተፍ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት አንድ ድምጽ ዋጋ እንዳላት ያመላከተበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የምርጫ አስፈጻሚዎችም ቢሆኑ በሰለጠኑት ስልጠና መሰረት ምርጫውን ያለምንም የጸጥታ ችግር ነጻ፣ ፍትሀዊ፣ ገለልተኛ በሆነ መልኩ በማከናወናቸው ለህዝቡም ለምርጫ አስፈጻሚዎችም ምስጋና ሊቸራቸው ይገባልም ብለዋል።

ይህም ሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የዲሞክራሲያዊ ስርዓቷ እያደገ መምጣቱን የዘንድሮ 7ኛው ምርጫ ማሳያ መሆኑን ነው ምሁራኑ የጠቆሙት።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ህዝቡ የሰጠውን ድምጽ በተገቢው ማክበር ይገባቸዋል ያሉት ምሁራኑ፤ በመገናኛ ብዙሀን አየተሰጡ ያሉ ምርጫውን የማክበር ሂደት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን