በግብርና ትራንስፎርሜሽን ላይ የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ

የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ ማነቆ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከግብርና ግንኙነት አካላት አማካሪ ካዉንስል ጋር በጅንካ ከተማ ዉይይት አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ እንደገለጹት፤ ግብርና የሀገር ኢኮኖሚ መሰረት በመሆኑ ባለፉት ጊዜያት በግብርናዉ ዘርፉ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ለዉጥ እየተመዘገበ ቢሆንም የአየር ንብረት ለዉጥና ሌሎች ተግዳሮቶች ለግብርና ስራዉ ማነቆ በመሆናቸዉ የምርምርና የአካዳሚክ ተቋማት የግብርናዉን ትራንስፎርሜሽን ስራ ከዳር ለማድረስና ለችግሮች መፍትሄ በመስጠት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የጎላ ስለሆነ በጋራ መመካከሩ ለግብርናዉ ስራ ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡

የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ፤ ግብርና ብዙ ኃላፊነት ያለበትና በሀገር ደረጃም ትልቅ አስተዋፅኦ ከሚያበረክቱ ተቋማት መካከል ከ32 በመቶ በላይ የሚሸፍን ሲሆን ይህ መድረክ በግብርና ሥራ ላይ በምርምር የሚሠሩ ተቋማት በጋራ በመወያየትና በመመካከር ለግብርናው ሥራ ማነቆዎችን በመለየት እንዲፈታ የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑን ገልፀዉ በዚህም በሰብል፣ በእንስሳት፣ በቡናና በተፈጥሮ ዘርፍ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የአርባምንጭ እፅዋት ጥበቃ ማዕከል ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም መርሻ በበኩላቸው፤ እንደሀገር ከተረጂነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ግብርና የራሱን ሚና እየተጫወተ ባለበት በሰብል ምርቶችና በእንስሳት ላይ የሚፈጠሩ በሽታዎችንና ተባዮችን ለማጥፋት የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በማሻሻል፥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና የቅድመና ድህረ ምርት አያያዝን በማሻሻል ውጤታማ ስራዎች እንዲሠሩ በጋራ በመመካከር የተጀመረውን ጉዞ ለማሳለጥ የሚረዳ መድረክ መሆኑን አመላክተዋል።

በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የግብርና ግብዓት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ግዳልቅ አልቅሚ፤ የጋራ ምክክር መድረኩ አካላት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የመንግስት የትኩረት አቅጣጫን መሠረት በማድረግ የኤክስቴንሽን ሥራዎች ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመለየት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ርብርብ እንደሚያደርጉ ጠቁመው በቀጣይ መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ባደረገባቸው በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሁም በኤክስፖርት ምርት በሚሠራው ሥራ ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ተሳታፊ አካላትም በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ተቀናጅተው በትጋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ራሔል አብራሃም – ከጂንካ ጣቢያችን