በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ከ93 ሺ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውንና ከ33 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መሰማራታቸውን የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ከ93 ሺ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውንና ከ33 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መሰማራታቸውን የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ

‎በዚህም ከ3.6 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አቅርቦት መሠራጨቱንና 3 ሺ 329 ሄክታር መሬት ለተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች መተላለፉም ተመልክቷል።

‎ቢሮው የግማሽ አመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ ወራት ትኩረት አቅጣጫ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲያከናውን የነበረው የምክክር መድረክ ተጠናቋል።

‎የቢሮው የግማሽ አመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በቀረበበት ወቅት፤ ባለፉት ስድስት ወራት 93 ሺ 345 ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውንና 33 ሺ 778 የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መሰማራታቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

‎በዚህም 327 ሚሊዮን 626 ሺ 444 ብር የብድር አቅርቦት መሠራጨቱንና 3 ሺህ 329 ሄክታር መሬት ለተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎችና ኢንተርፕራይዞች ተላልፏል።

‎በቀጣይ ወራትም ለ157 ሺ 715 ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር 728 ሚሊዮን 428 ሺህ 544 ብር ብድር ለማሰራጨትና 569 ሚሊዮን 247 ሺህ 059 ብር ብድር የማስመለስ ስራ እንደሚሰራ በሪፖርቱ ቀርቧል።

‎የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት ከስራ እድል ፈጠራ አኳያ በዞኖች የስራ ባህልን በማዳበር በግብርናው ዘርፍ በተሰራው ስራ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውንና በቀጣይም በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶችን መደገፍ ከተቻለ በዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም ማምጣት እንደሚቻል አንስተዋል።

‎የኦሞ ባንክ ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሀይለ ጊዮርጊስ እንዳሉት፤ ባንካችን ከ720 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለማሰራጨት ያቀደ ሲሆን ዕቅዱን ወደ 1 ቢሊየን በማሳደግ ለማሰራጨት እየሰራን ነው ብለዋል።

‎ዜጎች ተበድረው ሰርተውና ቆጥበው ሀብት ማፍራት እንዲችሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ ስራ ይጠይቃል ያሉት አቶ አለማየሁ፤ ውዝፍ እዳ አመላለስ ጋር ተያይዞ በሙሉ አቅም ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

‎በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በበኩላቸው፤ በወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ረገድ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከቀለም ትምህርት ባሻገር የሙያ ክህሎት ላይ ትኩረታቸውን እንዲያጠናክሩ ማድረግና ተቋማቱን ህዝብን በማሳተፍ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

‎የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ፤ የአገልግሎት ዘርፎችንና ኢንተርፕራይዞችን ገበያ መር አድርጎ መምራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

‎በተለይም አምራቾች እሴት እየጨመሩ እንዲሰሩ ማበረታታትና የገበያ ትስስርን ማጠናከርና የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን ማስፋፋት አስፈላጊ ነው ብለዋል ዶ/ር አበባየሁ።

‎የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በማጠቃለያ መልእክታቸው፤ በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ያለንን ጸጋና ሀብት አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮችና ተግዳሮቶች በመለየት የተጠናከረ ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

‎የዜጎችን ህይወት ለመቀየር በስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ መፍጠን፣ መፍጠርና መዝለል ይገባናል ሲሉ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በገጠርና በከተማ የኮሪደር ልማትና በሌማት ትሩፋት ረገድ የስራ አጦችን ተሳትፎ ማጠናከር እንደማያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

‎ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን