ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው የአምራች ድርጅቶች ቆጠረ እና ምዝገባ ጉልህ ሚና እንደሚኖር በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሆሳዕና ቅርንጫፍ አስታወቀ
የሆሳዕና ቅርንጫፍ የስታትስቲክስ አገልግሎቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና እና ወራቤ ለ1 ሺህ 6 መቶ 60 መረጃ ተሰብሳቢዎች ለ10 ቀናት የሚቆይ አቅም የማብቃት ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሆሳዕና ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን አሰፋ ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት፤ የአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ምዝገባ እንደሀገር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መጀመሩን ገልጸው በዚህም የአንደኛ ዙር ድርጅቶችን የመመዝገብ ሂደት በስኬት ተጠናቋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው የአምራች ድርጅቶች ቆጠረ እና ምዝገባ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም አስታውቀዋል።
በአንደኛ ዙር መረጃ አሰባሰብ ወቅት ትልቅ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ተብሎ የተለዩ የልማት ድርጅቶችን የመለየት ስራ ተሰርቷል ብለዋል አቶ ካሳሁን።
መረጃ የማሰባሰቡ ተግባር በአምራች ድርጅቶች ያሉ የሰው ሀብት፣ የግብአት፣ ወጪ፣ የሚገኘው የገቢ መጠንና ችግሮችንና መልካም ዕድሎችን በመለየት ለቀጣይ የተሻለ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ አጋዥ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከዚህም ባለፈ የኢኮኖሚ ዕድገት ጂዲፒ ከደረሰበት በመነሰት በቀጣይ ለመተንበይ እና የ10 ዓመቱን ሀገራዊና ልማታዊ ዕቅድ ለማቀድ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑንም አቶ ካሳሁን አስገንዝበዋል።
መረጃ አሰባሰቡ በ3 ነገሮች ትኩረት ያደርጋል ያሉት አቶ ካሳሁን፤ መረጃ ሰብሳቢ ትክክለኛ መረጃ መሰብሰብ፣ መረጃ ሰጪው የሚሰጠው መረጃ ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅም መሆኑን አውቆ ተአማኒ እና ትክክለኛ መረጃ መስጠት እና የሚሰበሰበው መረጃ ከገቢም ሆነ ከሌሎች መረጃዎች የሚገናኝ ሳይሆን ለስታትቲስቲክስ አገልግሎት ብቻ እንደሚውል ህብረተሰቡ ግንዛቤ ሊኖረው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የመረጃ አሰባሰብ በልማት ድርጅቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን እና ትክክለኛ ያልነበረውን የጂዲፒ መረጃ ችግሮችን ለመቅረፍ የልማት አንቀሳቃሾች፣ መንግስትና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ያስችላል ብለዋል።
በመጨረሻም ስልጠናው የሁለተኛ ዙር መረጃ ተሰብሳቢዎች በብቃት ተልዕኮአቸውን እንዲወጡ ለማስቻል በልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም አቶ ካሳሁን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ: ደሳለኝ ታደሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የምዕራፍ-2 የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በአርባምንጭ ስልጠና መሰጠት ተጀመረ
የፍትህ ዘርፍ ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት በፍትህ ስርዓት ላይ የሚነሱ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ተጠቆመ
በስራ ቦታቸው ላይ የህፃናት ማቆያ ማዕከል መቋቋሙ ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዳስቻላቸው የማእከሉ ተጠቃሚ እናቶች ገለፁ