በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የምዕራፍ-2 የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በአርባምንጭ ስልጠና መሰጠት ተጀመረ

በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የምዕራፍ-2 የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በአርባምንጭ ስልጠና መሰጠት ተጀመረ
‎
‎ስልጠናውን በክልሉ ከሚገኙ 8 ዞኖች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 100 በላይ ሰልጣኞች ለ10 ተከታታይ ቀናት እንደሚወስዱም ተጠቁሟል።
‎
‎ሀገራችን ኢትዮጵያ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁለንተናዊ ለውጦችን ለማስመዝገብ የሚያግዝ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሀገራዊ የልማት አጀንዳን ቀርፃ እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ ይታወቃል።
‎
‎ከዚሁ አገራዊ አጀንዳ ጋር የሚናበብ እቅድ ተዘጋጅቶ ከዳር ለማድረስ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎትም ያላሳለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
‎
‎በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የአርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስሜ አንበሴ፤ አገልግሎቱ ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካት ተጨባጭና ወቅታዊ መረጃዎችን በመሰብብ ለሚመለከተው አካል ሲያደርስ መቆየቱን አብራርተዋል።
‎
‎ሁሉም ሰልጣኝ በትጋት እና በጥራት መረጃዎችን መሰብሰብ ይጠበቅብናል ያሉት አቶ ስሜ፤ የገጠር ትራንስፎርሜሽን፣ የዲጂታል ኢኮኖሚን በሚያሳልጡ ተግባራት ላይ ትኩረት ከማድረግ ባሻገር የመረጃን ሚስጥራዊነትን በመጠበቅ የሀገራችንን የለውጥ ግስጋሴ መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
‎
‎የጋሞ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪ እና የአስዳዳሪው ተወካይ አቶ ተስፋፂዮን ዘነበ በበኩላቸው፤ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና መሰረተ ልማት እድገት እውነተኛና ተአማኒነት ያለው መረጃ መሰብሰብ ወሳኝነት አለው ሲሉ አሳስበዋል።
‎
‎መረጃው ለሀገራችን ብሎም ለዞናችን እድገት ወሳኝ በመሆኑ አሰልጣኞች በስልጠናው ወቅትም ሆነ ከስልጠናው በኋላ በጥብቅ ዲሲፕሊን መመራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
‎
‎የአርባምንጭ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊና የከንቲባው ተወካይ አቶ መኮንን ጋትሶ፤ ቁልፍ የሆነውን ሀገራዊ ተልዕኮን ለማሳካት መረጃን በትክክል በመሰብሰብ ሀገራዊ ሀላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል ብለዋል።
‎
‎በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የውሀና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ተሰማ እንደተናገሩት፤ መረጃ መሰብሰብ ታላቅ ሀገራዊ አደራ በመሆኑ ለሀገራችን የኢኮኖሚ አቅም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለሚኖረው በእውቀትና በመረጃ ስራውን መስራት ያስፈልጋል፡፡
‎
‎በቆጠራው በከተማና ገጠር ሁሉንም የኢኮኖሚ ድርጅቶች የሚያካትት ሲሆን በተለይም ማምረቻ፣ ግንባታ፣ ማዕድን፣ ንግድ አገልግሎት ዘርፎች፣ መደበኛና ኢ-መደበኛ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም መካከለኛና ትላልቅ ድርጅቶች እንደሚካተቱ ጠቁመዋል።
‎
‎በስልጠናው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ 8 ዞኖች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 100 በላይ ሰልጣኞች ለ10 ተከታታይ ቀናት እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።
‎
‎ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
‎
‎
‎