በስራ ቦታቸው ላይ የህፃናት ማቆያ ማዕከል መቋቋሙ ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዳስቻላቸው የማእከሉ ተጠቃሚ እናቶች ገለፁ

በስራ ቦታቸው ላይ የህፃናት ማቆያ ማዕከል መቋቋሙ ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዳስቻላቸው የማእከሉ ተጠቃሚ እናቶች ገለፁ

ሀዋሳ፡ ጥር 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀቤና ልዩ ወረዳ የህፃናት ማቆያ ማዕከል በመቋቋሙ የመንግስት ስራቸውን በአግባቡ ተረጋግተው ለማከናወን እንዳስቻላቸው የማእከሉ ተጠቃሚ እናቶች ተናገሩ፡፡

በልዩ ወረዳው በተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሁለት የህፃናት ማቆያ ማዕከላት ተቋቁመዉ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ የቀቤና ልዩ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታወቀ።

ወይዘሮ ሰሚራ በድሩ፣ አሚራ ኤልያስና ሐሊማ ዘይኑ በቀቤና ልዩ ወረዳ በተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ባለሙያ ሲሆኑ በልዩ ወረዳዉ የህጻናት ማቆያ ማዕከል አገልግሎት በመስጠቱ ስራቸዉን ተረጋግተው እንዲሰሩ እንዳስቻላቸዉ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት መሰል ማእካላት ባለመኖራቸዉ ወደ ስራ በሚመጡበት ወቅት ህጻን ልጅ ይዘው ለመምጣት ይቸገሩ እንደነበር አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በማእከሉ የህጻናት መጫወቻና ማረፊያ ስፍራ በመኖሩ በእረፍት ሰዓታቸዉ እየሄዱ ልጆቻቸዉን በማየትና ጡት በማጥባት ተረጋግተው የመንግስት ስራዎቻቸዉን በአግባቡ እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

በማእከሉ የተሻለ አገልግሎት ቢኖርም ዉስንነት ባላቸዉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሊሰጠዉ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።

በማቆያ ማዕከሉ ህጻናትን ሲንከባከቡ አግኝተን ያነጋገርናቸዉ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት ማእከሉ አገልግሎት መስጠቱ እናቶች በስራዎቻቸዉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድርባቸዉ እገዛ እንደሚያደርግላቸዉ ተናግረዋል።

በማእከሉ በቀን በርካታ ህጻናት አገልግሎት ያገኛሉ ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ለህጻናቱ አስፈላጊ የሆኑ የንጽህና መጠበቂያ፣ የመጫወቻ ቁሳቁስ መኖሩን ገልፀዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፈቲሃ ሱልጣን እናቶች ልጆቻቸውን ለስድስት ወራት ጡት ማጥባት እንዳለባቸው በጤና ባለሙያዎች የተሰጠውን ምክረ ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ የወሊድ ፈቃዳቸው ሲያልቅ ሲቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በልዩ ወረዳዉ ከዚህ ቀደም ሲያጋጥም የነበረዉ የእናቶችን ችግር ግንዛቤ ዉስጥ በማስገባት ሁለት የህጻናት ማቆያ ማዕከል ተቋቁሞ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የገለፁት ኃላፊዋ ይህም ለእናቶች ትልቅ እፎይታን የሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የማእከሉ መኖር ለእናቶችም ሆነ ለህጻናት ጥቅም እንዳለው በመናገር እናቶች ተረጋግተዉ ስራቸዉን እንዲያከናዉኑ ህጻናቱም ሳይጎዱ ጡት እያገኙ እንደሚያድጉ ገልፀዋል።

የህጻናት ማቆያ ማዕከል እናቶች ጡት ለማጥባት ወደ ቤት ሲመላለሱ በስራ ላይ የሚደርስውን ጫና በማቃለልም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ወይዘሮ ፈቲሃ ገልፀዉ ማእከሉን ከልዩ ወረዳ እስከ ታችኛዉ የቀበሌ መዋቅር ለማስፋፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ሪያድ ሙሂዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን