ለግብርናው እድገት መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የግብርና አጋር አካላት ድጋፍ የማይተካ ሚና እንዳለው የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ

ለግብርናው እድገት መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የግብርና አጋር አካላት ድጋፍ የማይተካ ሚና እንዳለው የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ

በዞኑ በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም FSRP ድጋፍ የግብርና ልማት አጋር አካላት ግንኙነት አማካሪ ካውንስል የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ፤ የግብርና ልማ ለድህነት ቅነሳ ዘላቂ እና አስተማማኝ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የዳበረና ውጤታማ የሆነ የግብርና ልማት ባለድርሻ አካላት ግንኙነት አማካሪ ካውንስል መፍጠር እንደሚገባ ገልጸው ለዚህም በየጊዜው ምክክር ይደረጋል ብለዋል።

የተለያዩ የሰብልና የእንስሳት በሽታዎች፣ የኖራ አቅርቦት ማነስ፣ የእርሻ ማሽነሪ አቅርቦት ችግር እንዲሁም የመስኖ አዉታሮች ዉስንነት በካውስሉ ቀጣይ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በተካሄደው ግብርና ልማት አጋር አካላት ግንኙነት አማካሪ ካውንስል የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቦረና ቦላዶ፤ በምክክሩ ግብርና ማነቆዎችን በመለየት አማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦችን በማቅረብ የተቀናጀ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለአርሶ አደሩ የሚደረስበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል ብለዋል።

በጎፋ ዞን የFSRP ፕሮጀክት ተጠሪ አቶ ሰጥአርጋቸው ዘውዴ፤ በፕሮጀክቱ የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራትን ለመነሻነት አቅርበዋል።

ከሰብልና ቅመማ ቅመም ምርት ባሻገር የእንስሳትና አሳ ምርት ዝርያን ለማሻሻል በተሠራው ተግባር ከ10 ሺህ በላይ ላሞችና ጊደሮችን በመደበኛና በዘመቻ ማደቀል መቻሉን አብራርተዋል።

የእንቁላል ምርትን ለማሻሻል 4 መቶ 25 ሺህ በላይ የ1 ቀን ጫጩትና ከ4 መቶ 28 ሺህ በላይ የ45 ቀን ጫጩቶች ማሰራጨት መቻሉን በሪፖርቱ አመላክተዋል።

በሰብሎች ላይ የሚከሰቱ ተባዮችንና አረምን ለመቆጣጠር ሰፊ ስራ መሠራቱን የገለጹት አቶ ሰጥአርጋቸው፤ ከገጠር ትራስፎርሜሽን ረገድ ፕሮጀክቱ ባቀፈው መሎ ኮዛ ወረዳ የተሠሩ ተግባራትን ገለጻ አድርገዋል።

በወረዳው በማይዘሎና ባልጣ ቀበሌያት ዘመናዊ የግብርና ምርት ግብይት ማዕከል፣ በጋዛር ቀበሌ የድልድይ ግንባታን ጨምሮ የነባር መስኖ ግንባታዎች ጥገናና የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል።

ተሳታፊ የግብርና ልማት አጋር አካላት ግንኙነት አማካሪ ካውንስል አባላት በቀረበው ሪፖርት መነሻ ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ አስተያየት ሰጥተውበታል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን