በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሯል
የዓለም ቅርስና መገለጫ የሆነውን የጥምቀት በዓል ዕሴቱን ጠብቆ ማቆየትና ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ በበዓሉ ተናግረዋል።
በበዓሉ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀዲያና ስልጤ ሀገረስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልዓከ ህይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ፤ ምዕመናኑ ከጥምቀት በዓል የሚያስተምረውን ትህትናና ፍቅርን በተግባር በማሳየት ስርዓተ ህጉን መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመሆኑም አብሮነትን በማጠናከር በመቻቻል የአካባቢና የሀገርን ሰላም በመጠበቅ ህዝበ ክርስቲያኑ መመላለስ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ የተገኙት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ በበኩላቸው፤ ለህዝበ ክርስቲያኑ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው በዓሉ ከሀይማኖታዊ ስርዓት በሻገር በባህላዊ ዕሴቱ የዓለም ቅርስና የኢትዮጵያ መገለጫ በመሆኑ ጠብቆ ማቆየት ለመጪው ትውልድ ትውፊቱን ጠብቆ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል።
እነዚህንና ሌሎች ክብረበዓላትን ለማቆየት በሚደረገው እንቅስቃሴ እና ሌሎች ቤተክርስቲያኒቱ የምታነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከተማ አስተዳደሩ በትብብር እንደሚሰራ አቶ ሳሙኤል ገልፀዋል።
በበዓሉ የታደሙት የህብረተሰብ ክፍሎች የዘንድሮው የጥምቀት በዓል አብሮነትና ፍጹም መቻቻል የታየበት መሆኑን ገልፀው ይህንንም ዕሴት ለሀገር አንድነት መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በከተማው ሰላማዊ በሆነ መልኩና ድምቀቱን ጠብቆ መከበሩን አውስተዋል።
የቃል ኪዳን ታቦታቱ በካህናት፣ በዲያቆናት፣ በሰንበት ተማሪዎችና በምዕመኑ ዝማሬ፣ በማህሌት፣ በያሬዳዊ ዜማ፣ በመለከት ታጅበው ወደ መንበረ ክብራቸው አቅንተዋል።
ዘጋቢ: ሔኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
3ኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የክለቦች ሻምፒዮና የምድብ ድልድል ይፋ ሆነ
በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ተግቶ በመስራት ከድህነት መውጣት ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ኢትዮጵያን ለዘመናት ከቆየችበት ቁስል ለማላቀቅ ባለፉት የለውጥ አመታት በርካታ ፖለቲካዊ ተግባራት ማከናወኑን መቻሉ ተገለጸ