የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያሳየበት በመሆኑ ምዕመኑ ከዚሁ በመማር በፍቅር፣ በሰላምና በአብሮነት ሊኖር ይገባል ሲሉ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጻዲቅ ተናገሩ

የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያሳየበት በመሆኑ ምዕመኑ ከዚሁ በመማር በፍቅር፣ በሰላምና በአብሮነት ሊኖር ይገባል ሲሉ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጻዲቅ ተናገሩ

የጥምቀት በዓል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በድምቀት ተከብሯል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ መልከ ጻዲቅ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ የጥምቀት በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በየአመቱ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በድምቀት የሚከበር እንዲሁም በዩኒስኮ የተመዘገበ ብሔራዊ የአደባባይ በዓል ነው::

የጥምቀት በዓል መላው የሰው ልጅ የእዳ ደብዳቤው ተቀዶለት ነጻ የወጣበትና ሚስጥር የተገለጸበት እለት መሆኑን ጠቁመው፤ ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ከተንኮልና ከክፉ ስራዎችን በመራቅ ለልማት፣ ለሰላምና ለጽድቅ ስራ መትጋት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው በቤተ እምነቶችና በማህበረሰቡ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነትና አንድነትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በመላዉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ሰላም የሁሉም ነገሮች መሰረት በመሆኑ ለአካባቢያችንና ለሀገራችን ሰላም በጋራ መቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳትና የታመሙ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን ይገባል ሲሉም አቶ ላጫ አሳስበዋል።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር፤ ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ በድምቀት የሚከበርና ልዩ ትርጉም የሚሰጠው በዓል ነው ብለዋል።

በዓሉ ምዕመኑ እምነቱንና ማህበራዊ መስተጋብሩን የሚያጠናክርበት፣ ፍቅሩ የሚጨምርበት፣ የበደሉትን ይቅር የሚልበትና የበደለውን ይቅርታ የሚጠይቅበት ከመሆኑም ባሻገር ከክፋትና ከበደል ወጥተን ይቅር የምንባባልበትና አብሮነትን የምናስተምርበት ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።

ወልቂጤ ከተማ ረጅም እድሜ፣ ታሪክና ብዙ የተፈጥሮ ጸጋዎች ያሉት መሆኑን ያነሱት ከንቲባው፤ በከተማው የተጀመሩ የልማትና የሰላም ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር ምዕመኑ ከመንግስት ጎን በመቆም እገዛውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየትም፤ በዓሉ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በድምቀትና በሰላም ማክበር በመቻላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የአብሮነት መሆኑን አንስተው፤ ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር አቅመ ደካሞችን በመርዳትና በማገዝ ሊሆን ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ዝናሽ ሙሉጌታ – ከወልቂጤ ጣቢያችን