“ዳራሮ” (Daraaro)
የጌዴኦ ብሔር የአዲስ ዓመት ብስራት
በብሔሩ ቋንቋ “ዳራሮ”(Daraaro) አበባ ማለት ሲሆን በበዓሉ ማሳረጊያ ላይ ከማር፣ ከገብስና ከተቆላ ቡና የሚሠራ ጣፋጭ ምግብም ነው። ይህም ብሔሩ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን የኑሮ መስተጋብር የሚያንፀባርቅ እንደሆነ የባህል አባቶች ይናገራሉ። የጌዴኦ ማህበረሰብ የዛሬ አበባ የነገ ፍሬ ነው ብሎ ስለሚያምን ለአበባ ልዩ ቦታ ይሰጣል። ብሔሩ በዚህ ምክንያት በዓመት አንዴ ከታህሳስ መጨረሻ እስከ ጥር ወር መጨረሻ ዳራሮ ብሎ በመሰየም ያከብራል ይላሉ የባህል አባቶች።
ባህላዊ አባቶች እንደሚሉት “አዳ ያኣ” ከተሰኘው ጥንታዊና ቀዳሚ ባህላዊ ሥፍራ የሚጀምረው የበዓሉ አከባበር ለአንድ ወር የሚዘልቅ ሲሆን “ዳራሮ” (Darraro) በብሔሩ ዘንድ የአሮጌ አመት መሰናበቻና የአዲሱ ዓመት መባቻ ተደርጎ የሚወሰድ ልዩ ሥፍራ የሚሰጠው በዓል ነው። በዓሉ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያና ተስፋ መሰነቂያ የዕርቅና የይቅርታ በዓል ነው።
የጌዴኦ ብሔር አሁን ላይ ባሌ”(baalle) በተሰኘው ባህላዊ አስተዳደር የሚመራ ሲሆን ጋዲቾ ለ8 ዓመታት የብሔሩ መሪ ሆኖ ያገለግላል።
በዚህም ብሔሩ ለረጅም ዘመናት ዲሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር መሠረት ባደረገው በገዳ ሥርዓት እየተመራ እስከዛሬ መዝለቁን መረጃዎች ያሳያሉ።
በዓሉ ከዚህ ቀደም የነበረው የመንግስት ሥርዓት ለብሔር ብሔረሰቦች ምቹ ባለመሆኑ ለረጅም ዘመናት አደባባይ ሳይከበር ቢቆይም ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ሲከበር የዘለቀ በመሆኑ ጥንታዊ መሆኑን የባህል አባቶች ይመሰክራሉ።
”ዳራሮ” (Daraaro) የጥጋብና የመልካም ዘመን ማሳያ ተደርጎ ስለሚወሰድ በሁሉም በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ በደስታና በፌሽታ ይከበራል። አባገዳውም ቄኤ መንደሩን ሠላም ላደረገ ፈጣሪ (Mageno) እያመሰገኑ ቀጣይ ዘመን የሠላምና የጥጋብ እንዲሆን የሚመርቁበት በዓል ነው።
ከዚህም ሲያልፍ ዳራሮ በበዓሉ ዕለት ለብሔሩ ባህላዊ መሪ ጋዲቻ (Gadichcha) የሚቀርብ ምግብም ነው። “ዳራሮ”፦ ከማር፣ ከተቆላ ቡናና ገብስ ተለውሶ የሚሠራ የበዓሉ መከወኛና ማድመቂያ ምግብ እንደሆነ የብሔሩ የባህል አዋቂዎች ይገልፃሉ።
ብሔሩ ባህላዊ ትውፊታቸውን ሳይለቁ ለዘመናት የዘለቁ በርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ሲሆን እንደባህል አባቶቹ ይህ ዘመን አቆጣጠር መነሻ የሚያደርገው በአንድ ዓመት ውስጥ ያሉ አሥራ ሁለት ወራትን መሠረት በማድረግ ከዋክብትና ኮከብ (Urjena bakkalcha) መታየትና መጥለቅ ምክንያት በማድረግ ነው።
እያንዳንዱ ወር ከእርሻና ከተፈጥሮ ክስተቶች ጋር በማገናኘት ለቀጣይ ዘመን እርሻ ዝግጅት የሚደረግበት እንደሆነ ነው የባህል አባቶች የሚያብራሩት። ይህም ያለፈው ዘመን ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት ታሳቢ ተደርጎ በባህል አባቶች ይቀመራል። በዚህ መሠረት ዳራሮ በዓል የሚከበረው በብሔሩ መጀመሪያ ወር በሆነው ጥር ወይም በብሔሩ አጠራር “ባሌሣ” (Ba’leessa) እንደሆነ የባህል ድርሳናት ያስነብባሉ።
በዳራሮ ዕለት ሁሉም የብሔሩ ተወላጆች “ቆሎ”(Qolo)ና “ቆጵሶ”(Qophphiso) የተሰኙ ባህላዊ አልባሳት ለብሰው “ጋዳ ቢፎም ጋዳ ቢፎም ጋዳ ቢፎም” (Gada Biifoomi Gada Biifoomi Gada Biifoomi…) እያሉ ባህላዊ ዜማ በማዜም ባህላዊ ምግቦችንና መጠጦችን በመመገብ ለፈጣሪ ምስጋና፣ ለአባገዳው ሥጦታ በመስጠት በአንድነት ያከብሩታል።
በዓሉ ሁሉም የብሔሩ ተወላጆች ከያሉበት ተሰብስበው አደባባይ ላይ በተለያዩ ሁኔቶች የሚከበር ሲሆን “ፋጎ”(fago) የተሰኘውን የብሔሩን ታራካዊ አመጣጥ የሚያወሳ መዝሙር በአባገዳው አማካኝነት “ሀርሱን ፉሌ ሀዋጣ ገነነ ኖኦ ጅላቲ ሀዶ ሆሆ….(Harsun fulle Hawwaxxa genene no’o jilat hado)… እያሉ ያዜማሉ።
ከዚያም ሲልፍ የብሔሩ መሪ አባገዳው በብሔሩ አጠራር “ላላባ”(lalaba) የተሰኘውን አዋጅ በማውጣት ለቀጣይ ዘመን የብሔሩን ህገ መንግስት የመደንገግና ይፋ የማድረግ ሥርዓት ይፈፀማሉ። አዋጁ በማህበረሰቡ ውስጥ ከባህል ያፈነገጡና ፈጣሪን የሚያስቆጡ ተግባራት እንዳይፈፀሙ ገደብ የሚያበጅ ሲሆን ህጉን የሚጥስ ማንኛው ሰው እንደየጥፋቱ ቅጣት ይጠብቀዋል።
በበዓሉ ማሳረጊያ “ዳራሮ” የተሰኘው ከማር፣ ከቡናና ከገብስ ተለውሶ የተሠራ ጣፋጭ ምግብ ከአባገዳው እጅ በመቀበልና በመቅመስ ሁሉም የበዓሉ ታዳሚዎች ምርቃት ይቀበላሉ። እርስበርስም በብሔሩ ቋንቋ “ዳጋሳኔአና ናጌእክ ጌስሶኦ” (dagasanne’a nage’ik geesiso’o) ወይም ለከርሞ በሠላም ያድርሰን ተባብለው የበዓሉ መቋጫ ይሆናል።
የዘንድሮው ዳራሮ በዓል በዞኑ በተለያዩ መዋቅሮች እየተከበረ ሲሆን፣ በዞን ደረጃ በዲላ ስታዲየም የክልልና ፌዴራል እንግዶች በተገኙበት ጥር 30/2018 “ዳራሮ ለባህልና ለቱሪዝም ልማት” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ይጠበቃል።
መልካም በዓል!
አዘጋጅ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የከተራና የጥምቀት በዓል በደመቀና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
ሰልጣኞች የህግ አወጣጥና አተገባበር ላይ በንድፈ ሃሳብ እንዲሁም በተግባር ያገኙትን ስልጠና በመደመር በዘርፉ ውጤታማ ስራ መስራት እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት የነበረው አለመግባባት በሰላም መፈታቱን ተከትሎ የእርቀ ሠላም ማጠቃለያ ኮንፈረንስ ተካሄደ