በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የከተራና የጥምቀት በዓል በደመቀና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
የከተማ አስተዳደሩ ለበዓሉ ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት በማስመልከት ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ የጥምቀት በዓልን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ በሰጡበት ወቅት፤ በዓሉ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱና የአደባባይ በዓል መሆኑን ጠቁመው በዓሉ በርካቶች በጉጉት የሚጠብቁት ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ሁነቶች የሚንፀባረቅበት ነው ብለዋል።
የዘንድሮው በዓል የሚከበረው በከተማው 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ህዝቦች ቀን በዓል እና የመሳሰሉ በርካታ ሀገራዊና ክልላዊ ሁነቶችን በስኬት ባስተናገደበት፣ ከተማው በኮሪደር ልማት ባሸበረቀበት እና የተለያዩ መሠረተ ልማቶች እየተፋጠኑ ባሉበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ከንቲባው ይህም በዓሉ ከሌሎች ዓመታት በደመቀ መልኩ እንዲከበር ያስችላል ብለዋል።
ከተማው ህብረብሔራዊ እና የሰላም አምባሳደር በመሆኑ በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማው ለሚመጡ እንግዶች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና ማረፊያዎች ልዩ ልዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ እንግዶችን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት ከንቲባው።
በበዓሉ ታቦታት ከማደሪያቸው ወጥተው በሰላም እስኪገቡ ከሰላምና ፀጥታ ጋር በተያየዘ በየደረጃው ካሉ የፀጥታና ከሀይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንዳለ ያውሱት አቶ ሳሙኤል፤ ሰላም ወዳዱ ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እና ለታቦታቱ ቅድሚያ በመስጠት የተለየ እንቅስቃሴዎችን ሲያስተውል ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በማድረስ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
እንደ ጥምቀት ያሉ መሰል የአደባባይ በዓላት የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር በመግለጫቸው የተናገሩት ከንቲባው፤ የንግዱና መላው ማህበረሰብ በተለመደው ኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ስርዓትና በጨዋነት እንግዶችን ማስተናገድ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ሆሳዕና ከተማ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ የከተሞች ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎችን እየተገበረ እንደሚገኝ የተናገሩት ከንቲባው፤ ወደ ከተማው በመምጣት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የከተራና የጥምቀት በዓል ለመላው ህዝበ ክርስቲያን የሰላምና የፍቅር እንዲሁም የአብሮነት እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
“ዳራሮ” (Daraaro)
ሰልጣኞች የህግ አወጣጥና አተገባበር ላይ በንድፈ ሃሳብ እንዲሁም በተግባር ያገኙትን ስልጠና በመደመር በዘርፉ ውጤታማ ስራ መስራት እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት የነበረው አለመግባባት በሰላም መፈታቱን ተከትሎ የእርቀ ሠላም ማጠቃለያ ኮንፈረንስ ተካሄደ